Popular Posts

Sunday, April 15, 2018

እምነትና ጥርጥር

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡22-23
ለእግዚአብሄር አንድን ነገር ማድረግ ከፈለግን በእምነት መሆን አለበት፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምንገናኘው በእምነት ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የምንቀበለው በእምነት ነው፡፡ ካለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡
ጥርጥር ደግሞ እግዚአብሄርን አለማመን ነው፡፡ ጥርጥር የእምነት ተቃራኒ ነው፡፡ ጥርጥር የእምነት ጠላት ነው፡፡ ጥርጥር እጃችንን ዘርግተን አንድን ነገር ከእግዚአብሄር በእምነት እንዳንቀበል እጃችንን እንድንሰበስብ ይፈታተነናል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ሲያምን የእምነት ጠላት የሆነውን ጥርጥርን መዋጋት አለበት፡፡
እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ሰው አንድን ነገር ሲያምን ያመነው ነገር እስኪሆን ደርስ በእምነቱ ፀንቶ መጠበቅ አለበት፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
የሚታየው ነገር ሁሉ የሚመጣው ከማይታየው አለም ነው፡፡ ሰው በማይታየው አለም ውስጥ በእምነት ያየው ነገር ወደሚታየው ግኡዙ አለም እስኪመጣ መታገስ አለበት፡፡
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ዕብራውያን 11፡1፣3
ሰው አንድን ነገር ሲያምን ያመነው ነገር ወደ ገሃዱ አለም አሰኪገለጥ ድረስ በጥርጥር ይፈተናል፡፡ ሰው ያመነው ነገር ትክክል እንዳይደለና እንዲተወው ጥርጥር ይፈትነዋል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የሚከፍለው በእምነቱ ብቻ ነው፡፡ የሚጠራጠር ሰው ከእግዚአብሄር አይቀበለም፡፡
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8
መጠራጠር የለብንም ማለት ግን የጥርጥር ሃሳብ ወደ አእመሮዋችን አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ሰው ያመነው ነገር እንደማይሆን ሰይጣን የጥርጥርን ሃሳብ ይልካል፡፡ ሰው የጥርጥርን ሃሳብ ከተቃወመው በእምነቱ ከእግዚአብሄር ብድራትን ይቀበላል፡፡ ሰው ግን የጥርጥርን ሃሳብ ከተቀበለው እምነቱ ያለፍሬ ይቀራል፡፡
ሰው መጀመሪያ ማመኑ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው ሲያምን ጥርጥርን በሚገባ መቃወም አለበት፡፡
ጴጥሮስ የጌታን ቃል እምኖ በውሃ ላይ መራመድ ጀምሮ ነበር ፡፡ ነገር ግን ጥርጥር በውሃ ላይ መራመድ የጀመረውን ጴጥሮስን አሰመጠው፡፡ ጴጥሮስ አይኑን ና ከሚለው ከኢየሱስ ቃል ላይ እንስቶ ወደወጀቡ ላይ ሲያደርግ መስመጥ ጀመረ፡፡
እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ማቴዎስ 14፡29-30
ጥርጥርን የምንዋጋው የእግዚአብሄርን ቃል በቀጣይነት በመስማት በማሰላሰልና በመናገር ነው፡፡ ጥርጥርን የምንዋጋው ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ነገር ባለመስማትና ባለመከተል ነው፡፡  
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡22-23
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment