Popular Posts

Thursday, January 4, 2018

ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ

ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡32-34
ብናገባም ባናገባም ልባችን ለጌታ ያለን ፍቅር እንዲከፋፋል እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ እኛ በዋጋ የተገዛን ነን የራሳችን አይደለንም፡፡ ስለዚህ በሁለንተናችን እግዚአብሄርን ማክበር አለብን፡፡
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20
ክርስቶስ ለእኛ ሞቷል፡፡ ክርስቶስ የሞተልን ወደፊት ለራሳችን እንዳንኖር ነው፡፡ ክርስቶስ የሞተልን ለሞተልን ለእርሱ እንድንኖርለት ነው፡፡ ስለዚህ ለእኛ ለሞተውና ለተነሳው እንጂ ወደፊት ለራሳችን መኖር የለብንም፡፡
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
ጌታ ቀናተኛ አምላክ ነው፡፡ አግብተንም ይሁን ሳናገባ ለጌታ የምንሰጠውን ስፍራ ለሚስታችን ወይም ለባላችን እንድንሰጠው ጌታ አይፈልግም፡፡
እንዲያውም ጌታን ሙሉ ለሙሉ ለመከተል ሚስታችንንና ባላችንን መጥላት ይኖርብናል፡፡ መጥላት ማለት ለጌታ የምንስጠው ፍቅር ለባላችን ወይም ለሚስታችን አለመስጠት ማለት ነው፡፡ ወይም ለባላችን ወይም ለሚስታችን ለጌታ ከምንሰጠው ፍቅር ያነሰ መስጠት ማለት ነው፡፡ የባል ወይም የሚስታችንን ፍቅር ከጌታ ፍቅር ካስበለጥነው ጌታን በሙላት መከተል ያቅተናል፡፡
ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ሉቃስ 14፡26
ጌታን አንደኛ ስንወደው ነው ባላችንን ወይም ሚስታችንን በሚገባ መውደድ የምንችለው፡፡ እግዚአብሄርንም አንደኛ ካልወደድነው ወይም ለእግዚአብሄር መስጠት ያለብንን ፍቅር ለባላችን ወይም ለሚስታችን ከሰጠን ነገር ሁሉ በህይወታችን ይመሰቃቀላል፡፡
ጌታ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለማንም ስጋ ለባሽ እንዳንሰጥ ወይም እንዳናካፍል ይፈልጋል፡፡ ለእርሱ ያለን ፍቅር የሚገባው እርሱና እርሱ ብቻ ነው፡፡
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡15
መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ማቴዎስ 22፡36-38
ስለዚህም ያገቡ ካገቡት ሰው በላይ የሚያስደስቱት ጌታ እንዳለ አድርገው ይኑሩ፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ያገባ #ያላገባ #ድንግል #ያገቡ #ያላገቡ #ፍቅር #ሚስት #ባል #ልብ #ተከፍሎአል #አላፊ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment