Popular Posts

Thursday, January 11, 2018

ዋጋው ይለያያል እንጂ በዚህም በዚያም ይሳካልሃል

የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። ኤርምያስ 15:19
የህይወታችንን እውነተኛ ስኬት የሚወስነው እይታችን ነው፡፡
ሰው ዋጋ በሚሰጠው በማንኛውም ነገር ሊሳካለት ይችላል፡፡ ለነገሮች የምንሰጠው ክብደትና ነገሮችን የምናይበት እይታ በአንዱ ወይም በሌላው እንዲሳካልን ያደርጋል፡፡ ለነገሮች የምንሰጠው ዋጋ ወይ በከበረው ነገር እንዲሳካልን ወይም ደግሞ በተዋረደው ነገር እንዲሳካልን ያደርጋል፡፡ አንዱ በተዋረደው አላማ ስኬት ሌላው ደግሞ በከበረው አላማ ስኬት ይሁን እንጂ ሁለቱም ስኬቶች ናቸው፡፡ የልጅነት ህልማችንን መፈፀምም ስኬት ነው በየእለት ኑሯችን እግዚአብሄርን ማስደሰትም ስኬት ነው፡፡ ዋጋው ይለያል እንጂ እኛ ራሳችን የምንፈልገው ነገር ላይ የመድረስ ስኬትን በተመለከተ ሊሳካልን ይችላል፡፡   
እግዚአብሄር የሚለው እውነተኛ ስኬት ላይ ለመድረስ ግን ብዙ መንገዶች የሉትም፡፡ እግዚአብሄር ስኬት የሚለው ስኬት ላይ ለመድረስ ግን ከአንድ በላይ መንገድ የለውም፡፡ እግዚአብሄር ስኬት የሚለው ስኬት ላይ ለመድረስ የከበረውን ከተዋረደው መለየትን ይጠይቃል፡፡ በከበረው እንዲሳካልህ የከበረውን መከተል ይኖርብሃል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡
እውነተኛ ስኬትን ለማግኘት እግዚአብሄር ከንቱ ነው ያለው ከንቱ ማለት እግዚአብሄር ዋጋ አለው ያለውን ዋጋ አለው ብሎ በቅንነት መቀበል ይጠይቃል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆነ ሰማያዊ ዋጋ ያለው ስኬትን ለማግኘት በየዋህነት እግዚአብሄር ይጠቅምሃል ያለውን ይጠቅመኛል ማለት አይጠቅምህም ያለውን አይጠቅመኝም ማለት ይጠይቃል፡፡
እግዚአብሄር የሚያየው ስኬት ውስጥ ለመግባት እውነተኛ ስኬት እንድ መንገድ ብቻ እንዳለው ማወቅ ይጠይቃል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
እንደ እግዚአብሄር መዝገበ ቃላት ስኬት እግዚአብሄርን በትግስትና በመሰጠት ፈፅሞ በመከተል ብቻ ይገኛል፡፡
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ማቴዎስ 16፡24
እንደ እግዚአብሄር አባባል ስኬት ለእግዚአብሄር ራስን በመስጠትና በእምነት ራስን ለእግዚአብሄር በመጣል ብቻ ይገኛል፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ማቴዎስ 16፡25
እንደ እግዚአብሄር እይታ ስኬት እግዚአብሄርን በነገር ሁሉ በማስቀደም ይገኛል፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
እንደ እግዚአብሄር ቃል ስኬት ሌሎቹን መንገዶች ሁሉ በመናቅ ይገኛል፡፡
ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ማቴዎስ 6፡24
እንደ እግዚአብሄር እይታ ስኬት የእግዚአብሄር ቃል በማመንና በመተግበር ይገኛል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራዊያን 11፡6
እንደ እግዚአብሄር እይታ የሆነ ስኬት ለአለም የማይመች ብዙዎችን የማይመርጡት በጥንቃቄ በመኖር የሚገኝ ዋጋን የሚያስከፍል ስኬት ነው፡፡
በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። ማቴዎስ 7፡13-14
እንደ እግዚአብሄር ከሆነ ስኬት በሰማያዊ እይታ መኖርንና ለሰማያዊ ጥሪ ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9
በአጠቃላይ እንደ እግዚአብሄር ሃሳብ የሆነ ስኬት ለእርሱ መኖር ነው፡፡
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #የተዋረደው #ስኬት #ዋጋ #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #መከተል #መሰጠት #ማስቀደም #እይታ #የከበረው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment