Popular Posts

Wednesday, September 6, 2017

ሳያቋርጡ መፀለይ እንዴት ይቻላል?

ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18
መፅሃፍ ቅዱስ ሳታቋርጡ ጸልዩ ብሎ ካዘዘ የምር ነው ማለት ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ካዘዘ ይቻላል ማለት ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ካለ መጠየቅ ያለብን እንዴት ነው የምችለው የሚለውን ብቻ ነው፡፡
ሰው ሳያቋርጥ መፀለይ የሚችለው ፀሎት ምን እንደሆነ ሲረዳ ነው፡፡ ፀሎት ምን እንደሆነ ያልተረዳ ሰው እንኳን ሳያቋርጥ ሊፀልይ ቀርቶ ምንም ሊፀልይም አይችልም፡፡
ተንበርክከን ወደ እግዚአብሄር የምንፀልይበት ጊዜ አለ፡፡ ቤታችንን ዘግተን የምንፀልይበት ጊዜ አለ፡፡ ድምፃችንን አውጠተን የምንፀልይበት ጊዜ አለ፡፡  ሁልጊዜ ግን በዚህ መንገድ መፀለይ አንችልም፡፡ በዚህ ሁሉ መንገድ መፀለይ የማንችልበት ጊዜ ይፈጠራል፡፡
ሳናቋርጥ ለመፀለይና በፀሎት ውስጥ ያለውን በረከት ተጠቃሚ ለመሆን በቀን ውስጥ ካለን የፀሎት ሰአት ውጭ መፀለይ መልመድ አለብን፡፡ ሳናቋርጥ በፀለይን መጠን ድላችን የማይቋረጥ ይሆናል፡፡   
ሰው ድምፁን ሳያሰማ በዝምታ ከራሱ ጋር ይነጋገራል፡፡ ፀሎት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገር ነው፡፡ ሰው ድምፁን ሳያሰማ በልቡ ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገር ይችላል፡፡ ሌላው ሳይሰማ ሰው እግዚአብሄርን ሊጠይቅ ከእግዚአብሄር መልሱን ሊሰማ ይችላል፡፡ ሰው በስራው ላይ እያለ ከእግዚአብሄር ጋር በልቡ ሊነጋገር ይችላል፡፡ 
ፀሎት ልብን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሄር ማንሳት ነው፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ይሰማል የሚባለው፡፡ ሰው በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ልቡን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሄር ሊያነሳ ይችላል፡፡ ሰው በዝምታ የእግዚአብሄርን እርዳታ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ሰው ሌላ የእለት ተእለት ስራውን እየሰራ የእግዚአብሄርን እርዳታ ሊፈልግ ይችላል፡፡
እውነት ነው ይህ ሁሉ ግን የሚጀመረው በርን ዘግቶ ከመፀለይ ነው፡፡ ሳያቋርጡ ፀሎትን የምንለማመደው ተንበርክከን ወደ ህልውናው ውስጥ መግባትን ከለመድን በኋላ ነው፡፡
አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴዎስ 6፡6
በስራ ቦታህም ሆነ ባለህበት ቦታ የምትፀልየው ያለማቋረጥ ፀሎት እልፍኝህን ዘግተህ ለምትፀልየው ፀሎት ተጨማሪ ይሆናል እንጂ የእልፍኝህን ፀሎት ሙሉ ለሙሉ አይተካውም፡፡
ሳታቋርጡ ጸልዩ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃል #ፀሎት #ልመና #ሳታቋርጡ #እልፍኝ #እግዚአብሔር #መኖር #እምነት #መስማት #መታዘዝ #በቃሉመኖር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment