Popular Posts

Saturday, September 16, 2017

መልካም ስራን መስራት ለመዳን ለምን አይጠቅምም?

ብዙ ሰዎች ለመዳን በመልካም ስራቸው ላይ ይደገፋሉ፡፡ መዳንን ሲያስቡ መልካም ስራዬ ያድነኝ ይሆንን ብለው ስለመልካም ስራቸው ጥንካሬ ይጨነቃሉ፡፡ መልካም ስራ መስራት እንደማያድን እና ሰው ለመዳን መልካም ስራ እንደሚያስፈገው ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሰው ጋር ህብረት ማድረግ እንዲችል ሰውን በመልኩ ፈጠረው፡፡ ሰው የተፈጠረው ወደ እግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ነበር ፡፡
እግዚአብሄር ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንዲኖር አስቦ ነው ሰውን የፈጠረው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖር ፣ ከእርሱ ጋር ህብረት እንዲያደርግና እንዲታዘዘው ነበር፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሄር ሰውን እንዲታዘዘው ያዘዘው በእርሱ ላይ ባመፀ ጊዜ እንደሚሞት ያስጠነቀቀው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ባልታዘዘ በዚያው ቅፅበት ሞተ፡፡ ሰው የተፈጠረበትን አላማ ሳተ፡፡ ሰው በአመፁ ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው የአባትና የልጅነት ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ተቆራረጠ፡፡ ሰው በራሱ ሆነ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት ሆነ፡፡
ስለዚህ ምክኒያት ምንም አይነት ለመዳን ወይም ለመጽደቅ የሚደረግ መልካም ስራ ሊያፀድቅ የማይችልበትን ምክኒያቶች እንመልከት፡፡
1.      ሰው ከእግዚአብሄር ክብር ወድቆዋል
በእግዚአብሄር መልክና አምሳል በእግዚአብሄር ክብር ተፈጥሮ ነበር፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 2፡27
ሰው ሃጢያትን ሲሰራ ከለእግዚአብሄር ክብር ወድቆዋል፡፡ ሰው ሃጢያትን ሲሰራ የእግዚአብሄን መልክ አጥቶታል፡፡ ሰው ሃጢያት በመሰራቱ ከእግዚአብሄር ክብር ጎድሎዋል፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ሮሜ 3፡23
ሰው ሃጢያት ሲሰራ ከእግዚአብሄ ክብርት ደረጃ ወደ ሳርነትና አባባነት ደረጃ ተዋርዶዋል፡፡ እግዚአብሄር በክብሩ የፈጠረው ሰው ከወደቀ በኋላ በሳርነትና በአበባነት ክብር የሚሰራው ስራ እግዚአብሄርን አያስደስተውም፡፡ እግዚአብሄር የአመፀኛ ምንም አይነት ስራ አያስደስተውም፡፡
ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡24
2.     ሰው ሃጢያት ሲሰራ ከእግዚአብሄር ቤተሰብ አባልነት ወጥቶዋል፡፡ 
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለህብረት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመጀመሪያ የፈጠረው ለህብረት እንጂ ለስራ አይደለም፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሄ ቤተሰብ ውስጥ ተፈጥሮዋል፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ወንድና ሴት ልጅ እንዲሆን ተፈጥሮዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የአባትና የልጅ ግንኘኙነት እንዲኖረው ተፈጥሮዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው የአባትና የልጅ ግንኙነት ሲቋረጥ ሰው አጣ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው ግንኙነት በሃጢያት ምክኒያት ሲቋረጥ ሰው እግዚአብሄርን የሚመስልበትን ባህሪ አጣው፡፡ እግዚአብሄር ያለመውን ህብረትና ግንኙነት ከሰው ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ሳይሆን ሰይጣንን በመስማቱ መልካም ባህሪ አጥቶ የሰይጣንን ባህሪ ተካፈለ፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሃንስ 8፡44
ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን የልጅነት ግንኙነት ያቋረጠውና የእግዚአብሄን ባህሪ ያጣው ሰው  በመልካም ስራ እግዚአብሄርን ሊያስደስተው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ስራውን ሳይሆን ግንኙነቱና የራሱን ባህሪ በሰው ውስጥ ማየቱን ነው፡፡ ግንኙነቱንና ህብረቱን አቋርጦ ባህሪውን ጥሎ ስራውን ልስራ የሚል ሰው እግዚአብሄርን አይማርከውም፡፡ 
3.     ሰው አላማውን ስቶዋል፡፡
ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን እየሰማና እየታዘዘ እንዲኖር ነው፡፡ ሰው ሃጢያት ሲሰራ የተፈጠረበትን አላማውን ሁሉ ስቶዋል፡፡ ሰው የተፈጠረው መልካም በሚላቸው ነገሮች እግዚአብሄርን እንዲያስደስት አይደለም፡፡ ሰው የተሰራው ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት በማድረግ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ የተፈጠረበትን የህብረት አላማ የሳተ ሰው በራሱ አነሳሽነት ነገሮችን በማድረግ እግዚአብሄርን ሊያስደስተው አይችልም፡፡
በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ሮሜ 8፡8
4.     ሰው በሃጢያቱ ምክኒያት ሞቶዋል፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ዘንድ ህያው ሆኖ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እያደረገ ለዘላለም እንዲኖር ነው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት ሲቋረጥ ሞተ፡፡ ንስሃ ያልገባና ኢየሱስን ያልተቀበለ በሃጢያት የሚኖር ሰው በእግዚአብሄር አይን ሙት ነው፡፡ ኢየሱስን የማይከተል ሰው ሰው ለእግዚአብሄር ህያው አይደለም፡፡ ሃጢያተኛ ሰው ይበላል ይጠጣል ይንቀሳቀሳል በእግዚአብሄር አይን ግን ሙት ነው፡፡ የሰው መንፈሱ ሞቶዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የሚገናኝበት የመንፈስ ክፍሉ ሞቶዋል፡፡ የሞተ ወይም የተለየ ሰው ማንንም ማስደሰት እንደማይችል ሁሉ ሃጢያተኛ ሰው እግዚአብሄርን በመልካም ስራ በፅድቁ ሊያስደስተው አይችልም፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን  2፡1-2
ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። ኢሳያስ 64፡6
5.      ሰው በሰይጣን ግዛት ውስጥ ውድቆዋል
ሰው እግዚአብሄርን እንቢ ሲል ሰይጣንን እሺ ብሎዋል፡፡ ሰው ለፈጠረው ለእግዚአብሄር ካልተገዛ ለሰይጣን ይገዛል፡፡ ሰው ወይ የኢየሱስ ተከታይ ይሆናል ወይም የሰይጣን ተከታይ ይሆናል፡፡ ከሁለቱም መካከል ነኝ የሚል ሰው የለም፡፡ ሰው በንስሃ ኢየሱስን ካልተቀበለ በሰይጣን ግዛት ውስጥ እያለ ኢየሱስን ሊያገለግል መልካምን ስራ ሊሰራ አይችልም፡፡  ሰው መልካምን ለመስራት መጀመሪያ ከተያዘበት ከዲያቢሎስ ግዛት ነፃ መውጣት አለበት፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን  2፡1-2
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
6.     ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር ጠላት ሆኖዋል፡፡
ሰው እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን በማድረጉ በእግዚአብሄር ላይ አምፆአል፡፡ ስለዚህ አመፀኛ የሆነ ሰው ላመፀበት መልካምን ነገር ከማድረጉ በፊት ከአመፁ ንስሃ መግባት አለበት፡፡ ከአመፁ ንስሃ ሳይገባና ሳይመለስ ከእግዚአብሄር ጋር ሳይታረቅ በጠላትነት የሚያደርገው መልካም ስራ ሁሉ ለመዳን በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሰው መልካመነ ስራ ከመስራቱ በፊት መታረቅ ግዴታ ነው፡፡
ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ሮሜ 5፡10
መልካምን ስራ መስራት ምንም ጉዳት የለውን ለመፅደቅ ወይም ለመዳን ግን አይጠቅምም፡፡ ሰው የሚድነው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራለትን ስራ ለእኔ ነው ብሎ በእምነት ሲቀበል ነው፡፡ መልካምን ስራ ለመስራት ከሞተ ስራ ንስሃ መግባትና እንደገና መመለድ ይጠይቃል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው ሁሉ መልካምን መስራት አለበት፡፡ ነገር ግን መልካምን የሚሰራው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #ደህንነት #መልካምስራ #መልካምምግባር #ሞት #አላማመሳት #ሐጢያት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ፍጥረት #ልጅነት #ስራ #እምነት #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment