Popular Posts

Friday, September 15, 2017

የልጅነት መንገድ

እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው የቤተሰቡ አባል እንዲሆንና ከእርሱ ጋር የአባትና የልጅ ህብረት እንዲኖረው ነው ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ልጁ እንዲሆን ነው፡፡ ሰውን የፈጠረው እግዚአብሔር ለሰው አባቱ ሊሆነው ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሰው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአምስት ቀን ውስጥ ሰርቶ በስድስተኛው ቀን ሰውን ፈጠረው፡፡ ሰው በስድስተኛው ቀን የተፈጠረው እንደ ልጅ ከአባቱ ጋር በሰባተኛው ቀን እንዲያርፍ ነው፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር የቤተሰብ አባልነቱና በልጅነቱ ለዘላለም እንዲኖር ነበር፡፡ ስለዚህ ነው እግዚአብሔር የተከለከለውን እንዳይበላ ሰውን ሲያዘው የምንመለከተው፡፡ እግዚአብሔር ለሰውን ልጅ ሆኖ ለዘላለም የሚኖርበትን መንገድ አሳየው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሰው ካልታዘዘ ከልጅነቱ እንደሚሻር ከእግዚአብሔር ጋር ያለው የአባትና የልጅ ግንኙነት እንደሚቋረጥ አስጠነቀቀው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ በመንፈሱ ሞተ፡፡ ሰው እግዚአብሔር ላይ በማመፁ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው የአባትነት እና የልጅነት ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ቤት ወጣ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ከአባቱ ጋር ተጣልቶ በመንፈሳዊ አነጋገር ጎዳና ተዳዳሪ ሆነ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር የሚመጡለት የቤተሰብ አባል መብቶችና ጥቅሞች ሁሉ ተቋረጡበት፡፡
ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላ፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ላይ አመፀ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ህልውና ራቀ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ተለየ፡፡ ሰው በራሱ ሆነ፡፡ በአዳም ሃጢያት ምክኒያት ሃጢያት በሰው ልጆች ላይ ሁሉ ወደቀ፡፡  
እግዚአብሔር ለዘላለም አብሮት እንዲኖር የፈጠረው ሰው ከእርሱ ለዘላለም እንዲለይና እንዲጠፋ አልወደደም፡፡ ኢየሱስን ወደምድር በመላክ የሃጢያትን እዳ ሁሉ እንዲከፍል አደረገው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የአባትነትና የልጅ ግንኙነት እንዲቋረጥ ያደረገውን የሃጢያትን እዳ በመስቀል ላይ በመሞት ሙሉ ለሙሉ እንዲከፍል አደረገው፡፡
አሁን የሃጢያት እዳ ሁሉ ተከፍሎዋል፡፡ አሁን እንደገና መታረቅ እንችላለን፡፡ አሁን ወደ ቤተሰቡ መመለስ እንችላለን፡፡
ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡18-19
ኢየሱስን እንደ አዳኛችንና እንደ ህይወታችን ጌታ ከተቀበልነው እግዚአብሔር መልሶ ልጅ አድርጎ ይቀበለናል፡፡  
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 1ኛ ዮሐንስ 4፡10
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። 1 ዮሐንስ 3፡1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #አቅርቦት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ጥሪ #ክህንነት #ስራ #መልክተኛ #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment