Popular Posts

Wednesday, September 13, 2017

የአዲስ ኪዳንን የነቢያትን አገልግሎት መረዳት

የነቢይነት አገልግሎት በጣም አስፈላጊ አገልግሎት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ነበሩ አሁንም በዚህ ዘመን ነቢያት አሉ፡፡
የብሉይና የአዲስ ኪዳን የነቢትነት አገልግሎት የተለያዩ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ በጥቂት አይነት ሰዎች ላይ ብቻ ነበር እንጂ በሁሉም የእግዚአብሔር ህዝብ ላይ አያርፍም ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ የሚያርፈው በነቢያት በነገስታትና በካህናት ላይ ብቻ ነበር፡፡
በዚህ በአዲስ ኪዳን ግን ኢየሱስ ወደምድር መጥቶ የሃጢያት እዳችንን ሁሉ በመስቀል ላይ በመሞት በመክፈሉ ምክኒያት መንፈስ ቅዱስ ንስሃ ገብቶ በተመለሰ ሰው ሁሉ ላይ ሊያርፍ ይችላል፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታቸው አድርገው በተቀበሉት ሰዎች ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ይኖራል፡፡
በአዲስ ኪዳን ዳግመኛ የተወለደ ክርስትያን ሁሉ እንደ ነቢይ እግዚአብሔርን በግሉ የመስማት ችሎታ አለው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ የእረኛው የኢየሱስ በግ የሆነ ሁሉ ድምፁን ይሰማል፡፡
ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። ዮሃንስ 10፡3
ክርስትያን በሙሉ ድምፁን የሚሰማበት ምክኒያት በደረጃችን ወርዶ ከሚናገረን ከእረኛ ችሎታ የተነሳ እንጂ ከሰሚዎቹ ችሎታ የተነሳ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በልባችን የሚኖረው እኛን በግል ሊመራን ነው፡፡  
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ሮሜ 8፡14
እግዚአብሔርን ሰምተን ለመታዘዝ ከተዘጋጀን እግዚአብሔር ይናገረናል፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ዮሃንስ 7፡17
እግዚአብሔር ስለህይወታችን እንደ ልጅ የሚናገረው ለእኛው ነው፡፡
እግዚአብሔር በግላችን የሚናገረንን ለማፅናትና ለመመስከር ነቢያትን ተጠቅሞ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የማይመሰክርልን እና የማያረጋግጥልንን ነገር በነቢያት ብቻ ተናግሮን ህይወታችንን አይመራም፡፡   
የነቢያት አገልግሎት ወሳኝ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን ትንቢትን መናቅ እግዚአብሔር በነቢያቱ ውስጥ ካስቀመጠውን በረከት እንድንጎድል ያደርገናል፡፡
የነቢይነት አገግሎት በቅዱሳን ህይወት ወሳኝ ቢሆንም ግን የነቢያት መልእክት እውነተኝነቱ መፈተሽ አለበት፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ትንትን እንድንመረምር ያስተምረናል፡፡
ጌታ ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን ስለሚኖር ማንኛውንም ትንቢት የመመርመር ችሎታው አለን፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ትንቢት አስፈላጊ በመሆኑ አትናቁ ያለው ሊያስት ስለሚችል ሁሉን ፈትኑ ያለው፡፡  
ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡20-21
ከእኛ ውጭ ስለህይወታችን ሃላፊነት የሚወስድ ማንም ነቢይ የለም፡፡ ስለህይወታችን ሃላፊነት ሊወስድ የሚችል በእግዚአብሔር ፊት የሚጠየቅልን ማንም ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው የለም፡፡ ፈትነን መልካሙን መያዝ ክፉውን መጣል የእኛ ብቻ ሃላፊነት ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነቢያት #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment