Popular Posts

Friday, August 25, 2017

ኃጢአት አይገዛችሁምና

ሃጢያት አስከፊ መንፈሳዊ በሽታ ነው፡፡ ሰዎች ለብዙ በሽታዎች መድሃኒት ሰርተዋል ለሌሎቹም በሽታዎች መድሃኒት ለመስራት እጅግ ይጥራሉ፡፡ ከበሽታዎች ሁሉ የከፋው በሽታ ደግሞ ሃጢያት ነው፡፡ ከእስራቶች ሁሉ አስከፊው እስራት የሃጢያት እስራት ነው፡፡ የሃጢያት መድሃኒት ያለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሰዎችን ከእግዚአብሄር የለየውንና ከአላማቸው ያሰናከላቸውን የሃጢያትን መድሃኒይት ለሰው ላመምጣት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ለማዳን ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
ከሃጢያት ካልዳንክ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ዋናውን አላማ ስተኸዋል ማለት ነው፡፡ ሃጢያት አሁንም የሚገዛህ ከሆነ ስለመዳን ያልተረዳኸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡   
ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡11-14
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለሁለት ምክኒያቶች ነው፡፡
ኢየሱስ ወደምድር የመጣበት ምክኒያት ከዚህ በፊት የሰራነውን ሃጢያት እዳ ለመክፈልና በደሙ ሃጢያታችንን ለማጠብ የሃጢያት ይቅርታን እንድናገኝ ስለሃጢያታችን በመስቀል መስዋእት ሊሆን ነው፡፡
በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ኤፌሶን 1፡7
ኢየሱስ ሃጢያታችን ይቅር ብሎን ብቻ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ከሃጢያት የበላይ የምንሆንበትን አሰራር ባያዘጋጅ ኖሮ ከሃጢያት የዳንን ሳንሆን ሃጢያት የሚገዛን ባዶ ሃይማኖተኞች ብቻ እንሆን ነበር፡፡
ኢየሱስ ግን ስለበፊቱ ሃጢያታችን እዳ መክፈል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ ተመልሰን በሃጢያት እንዳንኖር ሃጢያት የሚያሰራንን ስጋዊ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመስቀል ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው ለሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ሃጢያት እንዳይገዛን ሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመግደል ነው፡፡   
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለራሱ አይደለም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው እኛን ወክሎና ተክቶ ነው፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ የተሰቀለው የእኛን ሃጢያተኛ ስጋ ይዞና ተክቶ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተሰቅሎዋል፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ ሲሞት ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተገድሎዋል፡፡ አሁን ስጋዊ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
ሃጢያተኛ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡ ያልተረዳ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ የተታለለ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ አሁን ሃጢያት አይገዛንም፡፡
ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ የሚለው፡፡
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የሚያስመካው የእርሱ ጉልበት ሳይሆን ሃጢያተኛ ስጋው በመስቀል ላይ እንዲሰቀልና ከሃጢያት እንዲድን ያደረገው የእግዚአብሄር አሰራር እንደሆነ የሚናገረው፡፡
ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ስጋ #ስጋዊባህሪ #መስቀል #ኃጢያት #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment