Popular Posts

Monday, August 21, 2017

የዘላለም አምላክ

እግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም እስከዘላለም ነው፡፡ እግዚአብሄር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም እግዚአብሄር አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡  
አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ራእይ 22፡13
የእግዚአብሄር ከዘላለም እስከ ዘላለም መሆኑ በአእምሮዋችን እየመረመርም፡፡ የእግዚአብሄር ዘላለማዊነት በአእምሮዋችን ከመረዳት ያለፈ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዘለዓለማዊነት ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ያልፋል፡፡  
እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። ኢዮብ 36፡26
እግዚአብሄር የዘላለም አምላክነቱና እንደማይመረመርና ሰዎችም ሁሌ በእርሱ እንዲታመኑ የሚያዘው፡፡
አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡28
እግዚአብሄር የዘላለም አምላክና ማስተዋሉም የማይመረመር ስለሆነ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ የተሻለ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላከ ነው፡፡ የዘላለም ክንዶች ከእኛ በታች ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ የሚያኮራና ሳንናወጥ ረጋ ብለን እንንድንኖር የሚያደርግን እውቀት የለም፡፡  
መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡27
እግዚአብሄር በድንገት በህዝብ ድምፅ ብልጫ የተመረጠ ፕሬዝዳንት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡
መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። መዝሙር 145፡13
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። ኤርምያስ 10፡10
ከእግዚአብሄር ከዘላለም ከመኖር አንፃር የሰው በምድር ላይ ቆይታው እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ የሰውን በስጋ ቆይታ መፅሃፍ ቅዱስ ከእንፍዋለት ጋር ያነፃፅረዋል፡፡ የምድር ህይወት እጅግ አጭር በመሆኑ በራስ ላይ ከመደገፍ በላይ አክሳሪ ነገር የለም፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ በላይ ጥበብ የለም፡፡
ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14
ከእግዚአብሄር ዘላለማዊነት አንፃር የምድር ቆይታችን ነጥብ አትሞላም፡፡ የዘላለም አምላከ እግዚአብሄር አምባችን ነው፡፡   
ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። ኢሳያስ 26፡4
ሰው ማንንም ባያምን እግዚአብሄርን ማመን ግን ግዴታ ነው፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ካልተደገፍን በማንም ላይ መገደፍ አንችልም፡፡  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መኖሪያህእግዚአብሄር #እውቀት #ጥበብ #ሃይል #እንፍዋለት #አልፋ #ኦሜጋ #መጀመሪያ #መጨረሻ #ክርስትያን #አማርኛ #መደገፍ #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ፅድቅ #ማመን #አምባ #ስልጣን

No comments:

Post a Comment