Popular Posts

Sunday, August 13, 2017

ዘጠኙ የህብረት ጥቅሞች

የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ፈፅመን እግዚአብሄርን በሚገባ እንድናከብረው እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ዋና ዋና በረከቶች አንዱ የቅዱሳን ህብረት ነው፡፡ የወንድሞች መሰብሰብና ህብረት የእግዚአብሄርን ስራ ከምንሰራበት ቁልፍ መንገዶች አንዱ ነው፡፡
እግዚአብሄር ራሱን አባት አድርጎ መስጠት ብቻ ሳይሆን እህቶችና ወንድሞች ስለሚያስፈልጉን አውቆ የቅዱሳንን ህብረት ሰጥቶናል፡፡
በመጀመሪያይቱ ቤተክርስትያን ለህብረትና ለመሰብሰብ እጅግ ልዩ ትኩረት ከመስጠታቸው የተነሳ የቤተክርስትያን ጥንካሬና በህብረት ያገኙትን ውጤት እንመለከተናል፡፡
በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። ሐዋርያት 2፡46-47
በኢየሱስ ስም ህብረት ባደረግን መጠን ውጤታማነታችን እየጨመረ ስለሚሄድ ታላቁን ወንጌልን የመስበክ ተልእኮዋችንን በሚገባ መወጣት እንችላለን፡፡
በቅዱሳን ህብረት ብቻ ስለምናገኛቸው በሌላ በምንም መንገድ ግን ስለማናገኛቸው ታላላቅ ጥቅሞች እንመልከት፡፡ 
1.      የአንድነት አምልኮን ክብር የምንለማመደው ከቅዱሳን ጋር ተሰብስበን ነው፡፡  
በአንድነት ሆነን እግዚአብሄርን ማምለክ እጅግ ወሳኝና የክርስትና ህይወታችን የሚያለመለም ራሳችንን እንድንረሳና በእግዚአብሄር መንፈስ እንድንረሰርስና እንድንዋጥ የሚያስችለን ልዩ ልምምድ ነው፡፡ በአምልኮ የሚመሩንን ሰዎች የሰጠን ለህብረት እንጂ በግላችን አይደለም፡፡
ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙር 96፡6-7
2.     የፀጋ ስታዎች ተጠቃሚ የምንሆነው በህብረት ውስጥ ነው፡፡
በምንሰበሰብበት ጊዜ እግዚአብሄር በሌላው ወንድማችን በኩል የሚገልፀው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ህብረቱን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ይመጣል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተሰጠው ሌላውን ለማነፅ ፣ ለማፅናናትና ለመጥቀም ነው፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡26
ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡3
3.     የአገልግሎት ስጦታዎች የተሰጡት ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡  
እግዚአብሄር ስጦታዎችን ሐዋርያትን ፣ ነቢያትን ፥ ወንጌልን ሰባኪዎችን ፥ እረኞችንና አስተማሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ እድገታችንና ክርስቶስን ለመምሰል ብሎም ለአገልግሎት ለመታጠቅ እግዚአብሄር ለቤተክርስትያን የሰጣቸውን የአገልግሎት ስጦታዎች የምንጠቀመው በህብረት ውስጥ ነው፡፡
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡11-13
4.     ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ነው፡፡
እግዚአብሄር ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎች የሰጠው ለቤተክርስተያን ህብረት ነው፡፡ የሚያስተምሩን የሚመክሩንና የሚገስፁን በህብረት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ቆላስይስ 1፡28
ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ዕብራዊያን 13፡17
5.     የመንፈሳዊ ህይወት ደህንነታችን የሚለካው በህብረት ውስጥ ነው፡፡  
ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖራችንን የምናወቅው በህብረት ስንሆን ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወደ መንግስተ ሰማያት እየሄድን እንደሆነ የምናውቀው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡ ለወንጌል እንደሚገባ የማይኖረውን የምናቀናው በህብረት ሲገኝ ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወንድማችንን እንዳላሳዘንን የምናውቀው ከወንድማችን ጋር አብረን በመኖር፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል እየኖርን መሆናችንን እርግጠኛ የምንሆነው ብቻችንን በመኖር አይደለም፡፡ ትክክል መሆናችንን የምናውቀው የምንጠየቅለት ህብረት ሲኖር ነው፡፡ ስለ እውነተኝነታችንም ሰዎች የሚመሰክሩት በህብረት ስንገኝ ነው፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-18
የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ዕብራዊያን 13፡7
6.     ፍቅርን በተግባር የምንማረውና የምንረዳው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡
ፍቅር ለሌላው መልካም ማሰብ መናገርና ማድረግ ነው፡፡ ለብቻ ኖሮ ፍቅር አለኝ ማለት አይቻልም፡፡ የሚበድልና የሚታገሱት ባለበት ነው ፍቅርን የምንለማመደው፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ባለበት ህብረት ነው ፍቅርን ፣ ይቅር ማለትን እና ምህረትን የምንለማመደው የምናሳድገው፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው ሌላውን መቀበልና መውደድን የምንማረው፡፡
ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ኤፌሶን 3፡18-19
7.     በቅዱሳን ህብረት ስንገኝ ነው የጠፋውን የምንፈልገው፡፡
በቅዱሳን ህብረት ስንሆን ነው የጠፋውን የምናውቀው፡፡ በቅዱሳን ህብረት ስንገናኝ ነው የደከመውን ሸክም ለመሸከም መተያየት የምንችለው፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ 6፡1-2
8.     ከወንድማችን ፀጋ የምንካፈለው በመገናኘት ነው፡፡
እግዚአብሄር ባሳደገን ፀጋ ሌሎችን የምንመግበው ስንገናኝ ስናወራ ስንጫወት በቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄን ቃል ስንጫወት ነው በቃል ፀጋን የምንለዋወጠው፡፡ እግዚአብሄር ባሳደገኝ የህይወት ክፍል በምናገረው የፀጋ ቃል ነው ሌላውን የፀጋ ሃይል የማካፍለው፡፡ በህብረት ነው ሌላውን የምረዳውና ካለበትና ከተያዘበት የሚወጣበትን ፀጋ የማካፍለው፡፡   
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29
9.     ስንተያይ ነው አንዳችን አንዳችንን የምንሞርደው፡፡
በህብረት ነው ለፍቅርና ለመልካም ስራ የምንበረታታው፡፡ በህብረት ውስጥ ነው አንዳችን እንዳችንን የምንስለው፡፡ ስንገናኝ ነው አንዳችን የአንዳችንን የፍቅርና የመልካም ስራ ፍም የምናራግበው የምናነሳሳውና የምናቀጣጥለው፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡24-25
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment