Popular Posts

Saturday, April 8, 2017

ኢየሱስ በስጋ የመጣበት ዋናው ምክኒያት

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው በስጋ ነው፡፡ ኢየሱስ የመጣው ከሰው ልጅ ተወልዶ ሰው ሆኖ ነው፡፡
ኢየሱስ ሰው ሆኖ የመጣው በሰው የተሰራውን ሃጢያት በሰውነት ለመክፈል ነው፡፡
እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።  ሮሜ ሰዎች 5፡18-19
ኢየሱስ ከእኛ ስጋና ደም በመካፈል ወደ ምድር የመጣው ሰዎችን በፍርሃት ያሰረውን የሰይጣንን ሃይል በእኛ ምትክ እንደሰው በመሞት እንዲሽረው ነው፡፡
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራውያን 2፡14-15
ኢየሱስ በስጋ የመጣው አንድ የእግዚአብሄር ልጅ በአባቱ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለውን ክብር ሊያሳየን ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሰው በምድር መጥቶ ናሙናውን ባያሳየንና የእግዚአብሄር ልጅነትን ሞዴል ባይሆነን ኖሮ አንድ የሰው ልጅ ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን የአባትና የልጅ ግንኙነት ልንረዳው አንችልም ነበር፡፡
ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14
ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር የተመላለሰው እኛ ኢየሱስን የምንከትል የእግዚአብሄር ልጆች የበኩር ወንድማችንን ኢየሱስን እንድንመስል ስለተጠራን ነው፡፡
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ሮሜ 8፡29
ኢየሱስ እኛን ወንድሞቹን ሊመስለን የተገባው በተመሳሳይ መልኩ የምንፈተነውን ሊረዳን እንዲችል ነው፡፡
ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና። ዕብራውያን 2፡17-18
ኢየሱስ ሰው ሆኖ በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነው አሁንም በሰማይ በድካማችን ሊራራልን የሚችል ሊቀ ካህናችን እንዲሆን ነው፡፡
ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። ዕብራውያን 4፡15
ኢየሱስ በምድር ላይ አሸናፊ ሆኖ ተሳክቶለት የኖረው በሰውነቱ ነው፡፡ ኢየሱስ የአለምን መከራ ያሸነፈው እንደሰውነቱ ባይሆን ኖሮ አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ አይለንም ነበር፡፡   
በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። ዮሃንስ 16፡33
ኢየሱስ በምድር ላይ ጌታን ያገለገለው እንደ ሰውነት ባይሆን ኖሮ አብ እንደላከኝ እኔም እልካችኋለሁ ማለት አይችልም ነበር፡፡  
ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በሰውነት #በስጋ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ወንድሞቹን #የበኩርልጅ #መውደድ #መስጠት #መልካምነት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment