Popular Posts

Friday, April 7, 2017

ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ

ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡5
እግዚአብሄር ሰራተኛና ትጉህ አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሔርም፦ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ። ኤርምያስ 1፡12
እኛም በአላማችን ሁሉ ትጉህ እንድንሆንና ስራችንን ሁሉ ከልባችን እንድንፈፅመው እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ትጋትን የማያከብርና ለትጋት መልስ የማይሰጥ ነገር የለም፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ነገር ሁሉ በትጋት እንድንሰጥ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የጉልበት ቁጠባ ባንክ የለም፡፡ ጉልበታችንን ብንቆጥብ ለማንም ሳይሆን ይባክናል፡፡ ጉልበቴን አጠራቅሜ አንድ ቀን ትልቅ ነገር እገፋበታለሁ የሚባል ነገር የለም፡፡ መትጋትና ለጌታ ሃሳብ መድከም ጥቅምና ታላቅ እድል ነው፡፡ ለመትጋትና ለመድከም ያለን ብቸኛ እድል አሁን ነው፡፡ በህይወት እያለን ይህን እድል ካልተጠቀምንበት ተመልሰን አናገኘውም፡፡  
አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። መክብብ 9፡10
በክርስትና ህይወታችን እግዚአብሄር እንድንተጋ የሚፈልግባቸው 10 አቅጣጫዎች
·         በፀሎትና እግዚአብሄርን በማመስገን እንድንተጋ እግዚአብሄር ይፈልጋል
ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ፤ ቆላስይስ 4፡2
·         ወንጌልን ለመስበክና ትጋትን ይጠይቃል
ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡2
·         በስራ ቦታ ደሞዛችንን የሚከፍለንን እግዚአብሄርን በማየት ልንተጋ ይገባል
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ኤፌሶን 6፡6-7
·         የእግዚአብሄርን ቃል በማጥናት እንድንተጋ እግዚአብሄር ይፈልግብናል
የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡15
·         መልካምን ስራ ለመስራት ጉልበታችንን መቆጠብ የለብንም፡፡
ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። ገላትያ 6፡9
·         ለፍቅር ስራ መትጋታችንንና መድከማችንን እግዚአብሄር ይጠብቀዋል
በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥2-3
·         በቅድስና ለመኖር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ልንተጋ ይገባናል፡፡
ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡14
·         ደሃን ለመርዳት ልንተጋ ይገባናል
ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ። ገላትያ 2፡10
·         የእግዚአብሄርን ቃል ለማሰላሰል ልንተጋ ይገባል
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ 1፡8
·         የእግዚአብሄርን አላማ ለማግኘት እግዚአብሄርን በህይወታችን ለመፈለግ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
·         ለቅዱሳን ህብረት ልንተጋ ያስፈልገናል
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡24-25
የተስፋ ቃሉ ወደ እኛ እስከሚመጣ እውን እስከሚሆን በትጋት ልንፀና ይገባናል፡፡
በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። ዕብራውያን 6፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ትጋት #ስራ #መድከም #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትህትና #ልብ #እምነት

No comments:

Post a Comment