Popular Posts

Monday, April 3, 2017

መዳናችንንና ወደ መንግስተ ሰማይ እንደምንሄድ በእርግጠኝነት እናውቃለን?


በህይወት ዘመናችን እንደዳንንና አሁን ብንሞት ወደ መንግስተ ሰማይ እንድምንሄድ ሁላችንም እርግጠኛ መሆን እንፈልጋለን፡፡ አንዳንድ ሰው አይ ይህ የሚታወቀው አሁን አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ ሞተን መዳንና አለመዳናችን የምናውቀው የዚያን ጊዜ ነው ብሎ እድሉን የሚጠብቅ ሰው አለ፡፡ እግዚአብሄር ግን ይህን ታላቅ የመዳናችንን ነገር ለእድል አልተወውም፡፡ በጥርጥር በሁለት ሃሳብ እንዳንኖር ስለ ደህንታቸን ማወቅ የሚገባን ነገር ሁሉ በመፅሃፍ ቅዱስ ተጽፎዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስለመዳናችን በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ይናገራል፡፡
እግዚአብሄር ስለመዳናችን ሁሉንም ነገር በቃሉ አስታውቆን እያለ አንድ ጊዜ ሞቼ በትክክለኛ መስመር ላይ እንደነበርኩ አረጋግጣለሁ ማለት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ስንፍና ነው፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሄር ለመዳኛችን ያዘጋጀውን መንገድ ሳንከተል ቀርተን እግዚአብሄ ፊት ከቀረብን ሌላ እድል አይኖረንም፡፡ ዘመኔን ሁሉ የሄድኩት መንገድ የተሳሳተ ነው ብለን እንደገና እንደ አዲስ ልጀምር ማለት አንችልም፡፡
ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ ዕብራውያን 9፡27
እውነት እግዚአብብሄር የሚፈርድብን መልካም ስራቸው ነው ክፉ ስራቸው የሚበልጠው ብሎ ነውወይስ እግዚአብሄ በኢየሱስ ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ በመቀበላችን ወይም ባለመቀበላችን ነው ? 
መፅሃፍ ቅዱስ ስለመዳናችን ምን ይላል የሚለውን ማወቅ ከፀፀት ይጠብቀናል፡፡
ስለሃጢያቱ በመስቀል ላይ በሞተውና ሞትን ድል አድርጎ በተነሳው በኢየሱስ ያመነ ሰው የዘላለም ህይወት ህይወት አለው፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 1ኛ ዮሐንስ 5፡11-13
በኢየሱስ የሚያም ሰው ሁሉ የሃጢያት እዳው እንደተደመሰሰና ለሃጢያቱ ይቅር እንደሚያገኝ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ሁሉ በትንቢታቸው መስክረዋል፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ሐዋርያት 10፡43
በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ከሃጢያት ኩነኔ ነጻ ናቸው፡፡ በኢየሱስ በማመናቸው ብቻ ሃጢያት እንዳልሰሩ እግዚአብሄር ይቀበላቸዋል፡፡
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ሮሜ 8፡1
በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ከተለዩበት ሞት ወደ ህይወት ይሸጋገራሉ፡፡ ነፃ ናቸው አይፈረድባቸውምም፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። ዮሃንሰ 5፡24
በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ በሰሩት መልካም ስራ ሳይሆን ኢየሱስ በሰራላቸው የመስቀል ስራ በማመን ፅድቅን አግኝተዋል፡፡
እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ ሮሜ 5፡1
ኢየሱስ የሞተው ስለሃጢያታችን ነው፡፡ ከሞት የተነሳው እኛን የምናምነውን ለማፅደቅ ነው፡፡ እርሱን በማመናችን የእርሱ ፅድቅ ለእኛ እንዲቆጠርልን ነው፡፡
ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው።ሮሜ 4፡24-25
በኢየሱስ የሚያምኑ መዳናቸውና አለመዳናቸው እስኪሞቱና ስራቸው ተመዝኖ እስኪረጋገጥ የማይጠብቁት የዳኑት በፀጋ ወይም ነፃ ስጦታ ስለሆነ ነው፡፡ ሁሉ ሃጢያትን በመስራቱ ማንም በኢየሱስ በማመን እንጂ በስራ መፅደቅ ስለማይችል ነው፡፡
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። ኤፌሶን 2፡8-9
በኢየሱስ የሚያምኑ መዳናቸውን አሁኑኑ ያረጋገጡት የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ስለተሰጣቸው ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
የመዳናቸው ማረጋገጫው እግዚአብሄር መንፈሱን ስለሰጣቸው ነው፡፡   
አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ 8፡15
በኢየሱስ የመስቀል ስራ ያመነ ሰው የእግዚአብሄር መሆኑን ለማረጋገጥ የመንፈሱን ቀብድ ሰጥቶታል፡፡ የእግዚአብሄር ነው ተብሎ ታትሞበታል፡፡    
ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡22
በኢየሱስ የሚያምን ሰው እንደዳነ  የሚያረጋግጠው በውስጡ ያለው የእግዚአብሄር መንፈስ ስለሚመሰክርለት ነው፡፡ የአለም ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ አልዳንክም ከሚለው ድምፅ ይልቅ በውስጡ የሚመሰክርለት የእግዚአብሄር መንፈስ ምስክርነት ድምፅ ይበልጣል፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡14-16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እግዚአብሄር #ጌታ #ኢየሱስ #ቃል #መዳን #መንፈስቅዱስ #ሞቱናትንሳኤ #መስቀል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መንግስተሰማያት #መፅሃፍቅዱስ #ፍርድ #የዘላለምህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment