Popular Posts

Saturday, April 29, 2017

የጥበብ መጀመሪያ ምንጭ

ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ የሰው መረዳት ዝቅተኛው መመዘኛ እግዚአብሄርን መፍራቱ ነው፡፡ የሰው መረዳት የሚጀምረው ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት እንደሚኖር በማወቁ ነው፡፡ የሰው እውቀቱ የሚለካው በትንሹ ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና መስጠቱ በማወቁ ነው፡፡ የሰው እውቀቱ የሚታየው ከእግዚአብሄር ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት በመረዳቱ ነው፡፡ 
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ምሳሌ 1፡7
ሰው እጅግ የተዋጣለት የጠፈር ተመራማሪ ቢሆን ከእግዚአብሄር ጋር ግን እንዴት እንደሚኖር ካላወቀ ምንም አያውቅም፡፡ ሰው በሌላ በብዙ ነገር የተሳካለት አዋቂ ሆኖ ለፈጠረው ለእግዚአብሄር እውቅና መስጠት ካላወቀ ሀ ሁ አልቆጠረም ማለት ነው፡፡ ሰው በሌላ ነገር የተካነ ሆኖ ለክብሩ ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ስላለው ግንኙነት መረዳቱ ከሌለው ምንም አያውቅም ማለት ነው፡፡ ሰው ምንም ቢያውቅ ለእግዚአብሄር ፈጣሪነትና ባለቤትነት እውቅና ካለሰጠ የእውቀት መጀመሪያ ላይ አልደረሰም ማለት ነው፡፡    
እግዚአብሄን መፍራት ግን ከድርጊት አይጀመርም፡፡ በድርጊታችን እግዚአብሄርን ለመፍራት መፍጨርጨር የለብንም፡፡ በድርጊታችን አግዚአብሄርን ለመፍራት የድርጊታችንን ምንጩን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ በንግግራችን እና በድርጊታችን እግዚአብሄርን ለመፍራት ንግግራችንና ድርጊታችን የሚመጣበትን ምንጩ አስተሳሰባችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡
መጽፅሃፍ ቅዱስ የማንኛውም ድርጊት ምንጩ ሃሳብ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ እንዲያውም ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንደዚሁ እንደሆነ መፅሃፍ ያስተምረናል፡፡ በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአንብሄርን የሚፈራ ሰው በንግግሩ እግዚአብሄርን ይፈራል፡፡ በአስተሳሰቡ እግዚአብሄርን የሚፈራ በራሱ በድርጊቱ እግዚአብሄርን ይፈራል፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
ስለዚህ ነው ኢየሱስ ፈሪሳዊያንን እናንተን የሚያረክሳችሁ ድርጊት ሳይሆን የልባችሁ ሃሳብ ነው እያለ የሚወቅሳቸው፡፡
ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡18-19
ሰው እግዚአብሄርን በእውነት የሚፈራው በሃሳብ ደረጃ ነው፡፡ ሰው በሃሳብ ደረጃ እግዚአብሄርን ከፈራ ከመቀፅበት በንግግርም ሆነ በድርጊት እግዚአብሄርን የመፍራት ህይወት ይኖረዋል፡፡ ሰው ግን በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአብሄርን ካልፈራና ስርአት አልባ ከሆነ በድርጊቱ እግዚአብሄን መፍራት አይችልም፡፡ ሰው ሰው አያየኝም ብሎ ክፉን ቢያስብ በንግግሩና በድርጊቱ ሰው ያየዋል፡፡  
ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል፡፡ ሉቃስ 11፡39
ስለዚህ በአስተሳሰባችን እግዚአብሄርን በመፍራት እግዚአብሄርን የመፍራት ህይወት ይኑረን፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ምሳሌ 1፡7
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ በአስተሳሰቤ አንተን እፈራለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ወደ አእምሮዬ የመጣውን ሃሳብ ሁሉ አላስብም፡፡ እግዚአብሄር ሆይ የማስበውን ማንኛውንም ሃሳብ አንተን በመፍራት አስባለሁ፡፡ እግዚአብሄ ሆይ እንደቃልህ ያልሆነን ሃሳብ ከአእምሮዬ አሽቀንጥሬ እጥላለሁ፡፡ አንደ ቃልህ ያልሆነውን ሃሳብ በአእምሮዬ አላስተናገድም፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በአስተሳሰብ ህይወቴ አንተን በመፍራት ወዳዘጋጀህልኝ በረከት ውስጥ እገባለሁ፡፡ ስላስተማርከኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም ፡፡ አሜን
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አእምሮ #ልብ #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment