Popular Posts

Friday, April 14, 2017

መስቀል የለሽ "ወንጌል"

የክርስትና ልቡ ያለው መስቀል ላይ ነው፡፡ መስቀል የሌለበት ወንጌል ልብ እንደሌለው አካል ነው፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እንደሞተ የማያስተምር እና በትምህርቶች ሁሉ ሞቱና መነሳቱ የወጡ ከሆነ ከርስትና አይደለም፡፡
የሰባኪዎች ፈተና ክርስቶስ እንደተሰቀለ መስበክ ትተው ወንጌሉን በጥበብ ብልጫ መከሸን ነው፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን አንደተሰቀለ እኛም መስቀላችንን ይዘን እንድንከተለው ካልሰበከ ተሳስቷል፡፡ ሃዋሪያው ግን ስብከቴ በክርስቶስና እርሱም በተሰቀለበት መስቀል ዙሪያ ብቻ እንዲሆን ወስኛለሁ ይላል፡፡  
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። 1 ቆሮንቶስ 2፡1-2
ማነንም ሰው የመለወጥ አቅም ስለሌለው መስቀል የለሽ ስብከቶችን ሰይጣን አይፈራም፡፡ ሰይጣን ስለመስቀል እስካልተናገራችሁ ድረስ የፈለጋችሁትን ሀይማኖት ያድላችኋል፡፡
የክርስትና ሃይሉ የመስቀሉ ቃል ላይ ነው፡፡
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሰቀል እኛም አብረን ተሰቅለናል፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ሲሞት እኛ ሃጢያታችን ይቅርታ አገኘን፡፡ እኛ እብረነው በተሰቀልን ጊዜ ከሃጢያተኛ ስጋችን ተሰቀለ፡፡
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
የሰው እውነተኛ ፈተና መስቀሉን በሞኝነት መቀበል ወይም አለመቀበል ላይ ነው፡፡
እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡23
የክርስትና የመጨረሻ አላማው የትንሳኤውን ሃይል መረዳት ነው
እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። ፊልጵስዩስ 3፡10-11
ሰዎች ሲስቱ የሚነሱት በመስቀል ላይ ነው፡፡
ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። ፊልጵስዩስ 3፡18-19
ለትውልድ የምናስተላልፈው የወንጌል ቃል ይህ ነው፡፡
እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3-4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ሞት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #መስቀል #ጠቦት #በግ #ደም #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ማለፍ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment