Popular Posts

Tuesday, March 7, 2017

ብቸኛ መልካም ገድል

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
ብዙ አይነት ገድሎች አሉ፡፡ ሰዎች ስለ ብዙ ነገሮች ከብዙ ነገር ጋር ይጋደላሉ፡፡ መልካም ገድል አለ መልካም ያልሆነ ገድል ደግሞ አለ፡፡
ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን የተጠራንለት አንድ ገድል ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ በማያሻማ አባባል በግልፅ የተቀመጠው መልካም ገድል አንድ ገድል ነው፡፡ ፍሬ ያለው የሚገባ ገድል አለ፡፡ ጊዜያችንን ጉልበታችንን እውቀታችንን ልናፈስበት የሚገባ ገድል አለ፡፡
ይህ ልንጋደልለት የሚገባው ፣ ህይወታችንን ልናሳልፍበት የሚገባውና ልንተጋለት የሚገባው መልካም ገድል የእምነት ገድል ነው፡፡ ምክኒያቱም እኛ ምንም ማድረግ ባልቻልንበት ጊዜና ደካሞች በነበረን ጊዜ ክርስቶስ ስለእኛ ሞቷል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ሃጢያችን ሙሉ ለሙሉ ዋጋ ከፍሏል፡፡  ክርስቶስ ስለእኛ ጠላታችንን ዲያለቢሎስን አዋርዶታል፡፡ አሁን እንደ አዲስ የምንሰራው ምንም ስራ የለም፡፡ እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንረታው ሃጢያት የለም፡፡ እኛ አሁን እንደ አዲስ የምናሸንፈው ጠላት የለም፡፡ በክርስቶስ ሃጢያት ድል ተነስቷል፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን ስልጣን በመስቀል ላይ ሽሮታል፡፡
አሁን ከእኛ የሚጠበቅብን ነገር ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሰራው ድል ላይ መቆም ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የተሰራልንን ድል ከቃሉ በመመልከት በዚያ ላይ መቆም ብቻ ነው የሚያስፈልገን፡፡ አሁን የሚጠበቅብን ብቸኛ ገድል በቃሉ ላይ በእምነት የመቆም ገድል ነው፡፡ አሁን የሚጠበቅብን ብቸኛ ገድል በቃሉ ላይ እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ አሁን የሚጠበቅብን ተጋድሎ በስፍራችን ላይ በእምነት የመቆም ተጋድሎ ነው፡፡
ገድሉንም መልካም የሚያደርገው ተሰርቶ ባለቀ ስራ ላይ ስለምንቆም ነው፡፡ ገድሉን መልካም የሚያደርገው በእምነት ከቆምን ድሉ ሁልጊዜ የእኛ እንደሆነ የተረጋገጠለት ተጋድሎ ስለሆነ ነው፡፡ ገድሉን መልካ የሚያደርገው ውጤቱ የታወቀ ተጋድሎን ስለምናደርግ ነው፡፡   
አሁን የሚያስፈልገን ነገር  በተከፈለልን ዋጋ በእምነት መመላለስ ነው፡፡ አሁን የሚጠበቅብን ቃሉን መፈለግ ፣ ቃሉን ማሰላሰል ፣ በቃሉ ከባቢ ውስጥ መቆየት ፣ ቃሉን መናገር ፣ ቃሉን ማድረግና በቃሉ ላይ የመቆም የእምነት ገድል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ልናደርግ የምንችለው ተፈፀመ ባለው በኢየሱስ የመስቀል ስራ ላይ በእምነት መቆም ብቻ ነው፡፡
መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment