Popular Posts

Saturday, March 25, 2017

አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሄር የሚመራበት ትንሽ የዝምታ ድምፅ

እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው እግዚአብሄርን እንዲሰማውና እንዲረዳው አድርጎ በመልኩና በአምሳሉ ነው የፈጠረው፡፡ ሰዎች ሁሌ እንዲረዱት እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ለመስማትና ፈቃዱን ለማወቅ ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እኛ ፈቃዱን እንድናውቅ ይፈልጋል፡፡  
እግዚአብሄር ደግሞ አንዳንዴ ሳይሆን ሁል ጊዜ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በስራ ላይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁል ጊዜ እየተናገረ ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት እግዚአብሄርን እንዲናገረን ማድረግ ሳይሆን እግዚአብሄርን መስማት ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንዴት እንደምንረዳ ማወቅ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሄርን የማይሰሙት እግዚአብሄር ስላልተናገረ ወይም እግዚአብሄር ፈቃድ ፈቃዱን ሰውሮት ሳይሆን እግዚአብሄር እንዲናገራቸው የሚጠብቁት በጣም አስደናቂና ድራማዊ መንገድ ስለሆነ ነው፡፡
ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሄር የሚናገር የሚመስላቸው በነጎድጉዋድ ድምፅ ከሰማይ በከፍተኛ ድምፅ ነው፡፡ እውነት ነው እግዚአብሄር እንደዚያም ይናገራል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እጅግ ለተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በዚያ መልክ አይናገርም፡፡
ኤልያስ እግዚአብሄርን በነፋስ ፣ በምድር መናወጥ እንዲሁም በእሳት ውስጥ ቢጠብቀውም እግዚአብሄር ግን ሰዎች በሚጠብቁዋቸው በነጎድጉዋድ ውስጥ አልነበረም፡፡
እርሱም፦ ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። 1ኛ ነገሥት 19፡11-12
መንፈሳችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያውቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ዳግም በተወለደው በመንፈሳችን ውስጥ የእግዚአብሄር ፈቃድ አለ፡፡ የእኛ ሃላፊነት ያንን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመረዳት ጊዜ ወስደም ልባችንን መስማት ነው፡፡ የእኛ ሃላፊነት ጊዜ ወስደን የመንፈስን ምስክርነት በልባችን ውስጥ መፈለግና መስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄን ፈቃድ ለመስማት ራሳችንን ስንሰጥ ትንሽዋን የለሆሳስ ድምፅ በልባችን መስማት እንችላለን፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡14፣16
የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንድናውቅ ተሰጥቶናል፡፡ ይህንን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምናውቀው በመንፈሳችን አማካኝነት ነው፡፡ ኢየሱስን ስንቀበል ከእግዚአብሄር የተወለደው መንፈሳችን የእግዚአብሄን ፈቃድ ያውቃል፡፡ ይህ በስንት ጊዜ አንድ ጊዜ የሚሆ ሳይሆን መንፈሳችን በሰማን ቁጥር የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምንሰማበት መንገድ ነው፡፡  
በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡11-12
ስለ አንድ ነገር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ስንፈልግ ልባችንን መስማት ያስፈልገናል፡፡ በልባችን የእግዚአብሄን አዎንታ ወይም አሉታ ምልክት እንፈልጋለን፡፡ በልባችን የእግዚአብሄርን የፈገግታ ወይም የተኮሳተረ ፊት እንፈልጋለን፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ስንፈልግ በልባችን መንፈሳዊውን የማስጠንቀቂያ ቀይ መብራት ወይም የይለፍ አረንጋዴ መብራት ለመለየት ጊዜ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡  
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ስለምንፈልግበት ነገር ስናስብ እና በፀሎት ልባችንን ለመስማት ጊዜ ስንወስድ ልባችን ወይ በሰላም ይሞላል ወይም ልባችን ይረበሻል፡፡ ለእግዚአብሄ ፈቃድ ልባችንን ስናዳምጥ ወይ ልባችን በደስታ ይሞላል ወይም ይኮሰኩሰናል፡፡ ስለዚህ ነው ለልባችን ሰላም ቅድሚያ መስጠትና በልባችን ሰላም ካልተሰማን የእግዚአብሄር ፈቃድ ስላይደለ ማድረግ የሌለብን፡፡ በልባችን ደሰታ ከፈሰሰና ሰላም ከተሰማን ደግሞ የእግዚአብሄር  ፈቃድ መሆኑን አውቀን ማድረግ ያለብን፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ቆላስይስ 3፡15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment