Popular Posts

Friday, March 17, 2017

ኢየሱስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡16
ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቀውም ይላል ሃዋሪያው፡፡ ግን ክርስቶስንም በስጋ አናውቀውም ማለት ምን ማለት ነው? ማንንም  በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለትስ?
ሃዋሪያው ቀድሞ ክርስቶስን በስጋ ያውቀው ነበር፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ አንድ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ አንድ ያገሩ ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ነበር የኢየሱስን ተከታዮች እንደሳቱ በማመን ሊገድልና ሊያስር ደብዳቤ ተቀብሎ ይሄድ የነበረው፡፡
ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሐዋርያት 9፡1-2
ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ክርስቶስን ከእግዚአብሄር እንዳልተላከ እንደተራ ሰው ማየት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት በእግዚአብሄር መመዘኛ  ሳይሆን በሰው መመዘኛ ኢየሱስን መመዘን ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት የኢየሱስን የዘር ግንዱን አይቶ መጣል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ኢየሱስ የሰው ልጅነቱን እንጂ የእግዚአብሄ ልጅነቱን አለማየት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት የሃገር ልጅ መሆኑን እንጂ ከእግዚአብሄር መላኩን አለመቀበል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት በእግዚአብሄር ዘንድ ያለውን ስፍራ አለማወቅ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ምክኒያት ፈልጎ መሰናከል ማለት ነው፡፡
ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። ማቴዎስ 13፡55-56
ጌታ ጳውሎስን በብርሃን ከተገናኘው በኋላ ግን ኢየሱስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ አቆመ፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ እንድ አይሁዳዊ ሳይሆን እንደ ጌታ ነው፡፡ አሁን ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ ተራ ሰው ሳይሆን እንደ አዳኝ ነው፡፡ አሁን ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ ማሪያም ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡   
እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፦ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው። ሐዋርያት 9፡6
ሃዋሪያው ይቀጥልና ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ይላል፡፡ ክርስቶስን ብቻ አይደለም ማንምም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ይላል፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በእግዚአብሄር መመዘኛ እንጂ በሰው መመዘኛ እንመዝንም፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በስጋ ማዕረጉ ሳይሆን በእግዚአብሄር ዘንድ ባለው የልጅነት ማዕረጉ ነው የምናውቀው ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በዘር ፣ ፆታና ቀለም አንለካም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በስጋ ባለው ክብር አናከብርም ፣ በስጋ ባለው ድካም አንንቅም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በምድራዊ መመዘኛ አናነሳምምም አንጥልምም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት እግዚአብሄር እንደሚያይ እንጂ ሰው እንደሚያይ አናይም ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡16-17
ሰውን ሁሉ የምናውቀው በክርስቶስ ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምንመዝነው በክርስቶስ ባለው ስፍራ ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምንቀበለው በክርስቶስ አቀባበል ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምናከብረው በክርስቶስ ክብር ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምናውቀው ክርስቶስ በሚያውቀው እውቀት ነው፡፡ ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡7
ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፡፡
ማንም ማንም ማንም
በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። ገላትያ 3፡26-28
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #ማንነት #የእግዚአብሄርንእይታ #በስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #በስጋደረጃ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ስፍራ #ማእረግ #ስልጣን

No comments:

Post a Comment