Popular Posts

Friday, March 3, 2017

ቃሉን የማሰላሰል 7ቱ ጥቅሞች

ቃሉን ማሰላሰል እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ሰው የዋጠው ምድሃኒት በሰውነቱ ካልቆየ እንደማይጠቅመው ሁሉ ቃሉን ካላሰላሰልነው አይጠቅመንም፡፡ ቃሉን ለረጅም ጊዜ ባሰላሰልነው መጠን ለረጅም ጊዜ ይጠቅመናል፡፡  
ቃሉን ማሰላሰል የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ። መዝሙር 77፡11-12
1.      ቃሉን ማሰላሰል በእግዚአብሄር ሃሳብ ክባቢ ውስጥ እንድንቆይ ይረዳል፡፡ ለምሳሌ አንደ ዘር ለመብቀል ከባቢው አመቺ መሆኑ ወሳኝ ነው፡፡ ዘር ለመብቀል እርጥበት ምቹን ሁኔታ እንደሚፈጥርለት ሁሉ የእግዚአብሄርን ቃል ማሰላሰል በእግዚአብሄር ሃሳብና ፈቃድ ውስጥ አንድንቆይ ምቹን ሁኔታን ይፈጥርልናል፡፡ በተቃራኒው የእግዚአብሄርን ቃል የማናሰላስል ከሆንን የእግዚአብሄር ፈቃድና ሃሳብ በህይወታችን ለመብቀል ፣ ለማበብና ለማፍራት ተስማሚ ሁኔታን አያገኝም፡፡ ቃሉን ሰምተን ብቻ የምንረሳው የማናሰላስለው ካልሆንንና በማስተዋል ለብዙ ጊዜ ከእኛ ጋር የማናቆየው ካልሆነ ሙሉ ፍሬን አይሰጠንም፡፡
በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። ማቴዎስ 13፡23
2.     ቃሉን ማሰላሰል ከቃሉ ውጭ እንዳናሰላስል ይጠብቀናል፡፡ ቃሉ ማሰላሰል የሰይጣንን ሃሳብ እንዳናስብ ይጠብቃናል፡፡
ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። መዝሙር 1፡2
3.     ቃሉን ስናሰላስል በመንፈስ እንድንሆን ይረዳናል፡፡ ቃሉን ማሰላሰል ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት ስስና ንቁ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ሮሜ 8፡5-6
4.     ቃሉን ማሰላሰል አግዚአብሄር እንዲናገረን መንገድ ይከፍትልናል ወይም እግዚአብሄር ሲናገር መስማት እንድንችል አቅምን ይሰጠናል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መለየት እንድንችል ይረዳናል፡፡ ቃሉን በትጋት ማሰላሰል የእግዚአብሄርን ፈቃድ ፈትነን እንድለይ ያስችለናል፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
5.     ቃሉን ማሰላሰል የእግዚአብሄርን ቃል እንድናደርገው ሃይል ይሰጠናል፡፡ የቃሉን ጥልቅ ትርጉም ማግኘት የምንችለው ስናሰላስለው ብቻ ነው፡፡ ስናሰላስለው ነው የቃሉን ብልት በትክክል በመበለት ልንከፋፍለው የምንችለው፡፡ ቃሉ በትክክል በከፋፈልነው መጠን ለመፈፀም እየቀለለን ይሄዳል፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ ኢያሱ 1፡8
6.     ቃሉን ማሰላሰል በሁሉ እንዲከናወንልን ያስታጥቀናል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የያስብ እንደ እግዚአብሄር ያስባል ይባላል፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ እንደሚከናወንለት ሁሉ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያሰላስል ሰው በነገር ሁሉ ይከናወንለታል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝሙር 1፡2-3
7.     ቃሉን ብቻ በማሰላሰል ልባችንን ከጠበቅን ህይወታችንን በንፅህና እንጠብቃለን፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝሙር 1፡1-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ቃል #ማሰላሰል #ማሰብ  #ስኬት #ክንውን #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት

No comments:

Post a Comment