Popular Posts

Friday, January 27, 2017

የቃልኪዳን ስምረት

ቃልኪዳን በአለም ላይ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ብዙ ወሳኝ ነገሮች የሚደረጉት በቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት በአለም ላይ ያለን ሃብትና እምቅ ጉልበት አለመረዳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት አላማን መሳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት ፍሬቢስ መሆን ነው፡፡
ቃልኪዳን በሁለት ወገኖች መካካል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ አንዱ ወገን ለሌላው ወገን የሚያደርግለት ነገር ሌላኛውም እንዲሁ ለሌላው የሚያድርገለት ነገር አለ፡፡
እኛ በብዙ ነገሮች የተወሰንን ስለሆንን ሁሉንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ለወሳኝ ነገሮች  የቃልኪዳን አጋር ያስፈልገናል፡፡ ቃልኪዳን ደግሞ በራስ ድርሻ ላይ ብቻ ማተኮርን ይጠይቃል፡፡
በአለም ላይ ያለው ችግር በራስ ሃላፊነት ላይ ያለማተኮር ችግር ነው፡፡ በአለም ላይ ያለው ግራ መጋባት የመጣው የስራ ክፍፍልን ካለመረዳትና የራስን ድርሻ ብቻ ፈፅሞ ካለማረፍ የሚመነጭ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ህብረትን ፈልጎ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እያደረገ ምድርን የሚያስተዳድርለትን የሚረዳውና የሚግባባው ፍጥረት ፈልጎ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ዘፍጥረት 1  
ሰው በሃጢያትም ከወደቀ በኋላ እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ለመድረስና አላማውን በምድር ላይ ለማስፈፀም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እግዚአብሄር በዘመናት መካከል ከአብርሃም ፣ ከኖህ ፣ ከእስራኤል ህዝብ ጋር ቃልኪዳን ሲያደርግ ነበር፡፡
አሁንም በዚህ ዘመን እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ መስዋእትነት ከእኛ ጋር ኪዳን ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር መንግስቱን የሚሰራለትና የሚያስፋፋለት ሰው ፈልጎ ከእኛ ጋር ቃልኪዳን ገብቷል፡፡
ነገር ግን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎችን ግራ የሚያጋባቸው የቃል ኪዳን የስራ ድርሻ ነው፡፡ አሁንም በዘመናችን ሰዎች እግዚአብሄር ወዳየላቸው የህይወት ከፍታ እንዳይገቡ የሚያግዳቸው የቃልኪዳንን ድርሻን አለመረዳት ነው፡፡
ለምሳሌ ሰዎች የሚበላና የሚጠጣ የሚለበስ በመፈለግ ህይወታቸውን የሚያባክኑት የእግዚአብሄርን አቅርቦት የቃልኪዳን ድርሻ ባለመረዳት ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
በዚህ የቃል ኪዳን ስምምነት መሰረት የሰው ድርሻ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ በእግዚአብሄ ፊት ትክክለኛ ነገር ማድረጉን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሰው ድርሻ እግዚአብሄን በምድር መወከል ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ደህንነት ማሰብ ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ማሸነፍና መስፋፋት መስራት ነው፡፡  የሰው ድርሻ የእግዚአብሄን ቤተክርስትያን በጎነት መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ የመንግስቱን አባላት መንከባከብና ማስነሳት ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ ስለሆነና በስጋ ውስጥ ስለማይኖር በምድር ላይ ይህንን እንድናደርግለት የጠራን እኛን ነው፡፡ እኛ ይህንን ማድረግ እንችላል፡፡ በዚህ ማድረግ በምንችለው ድርሻ ላይ ብቻ ብናተኩር ውጤታማ እንሆናለን እግዚአብሄርንም በሙላት አገልግለን እናልፋለን፡፡    
የእግዚአብሄ ድርሻ ደግሞ ለሰው የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማሟላት ነው፡፡ ይህንን እንዲህ አድርገው ብሎ የሚመክረው የለም፡፡ ይህን ደግሞ እርሱ ያደርገዋል፡፡
አሁን ሰው የተሰጠውን ይህንን በቂ ሃላፊነት ጥሎ እግዚአብሄር እንዴት እንደሚንካከበው ቁጭ ብሎ ቢጨነቅ ከንቱ ነው፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር ማድረግ አይችልምና እግዚአብሄር የሰጠውን መንግቱንና ፅድቁን የመፈለግ ሃላፊነቱን እየጣለ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኔን በትክክል ይይዘኝ ይሆን ብሎ ሲፈራ ድርሻውን መወጣት ያቅተዋል፡፡ እግዚአብሄር አያያዙን ያውቅበት ይሆን ብሎ ሰው ቢያወጣና ቢያወርድ ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡
ሰው በህይወቱ ይህን የቃል ኪዳን ሃላፊነት ካልተረዳና በራሱ ሃላፊነት ብቻ ላይ ካላተኮረ የእስራኤል ህዝብ የሴይርን ተራራ እንደዞሩት ይዞራል እንጂ እግዚአብሄር ወዳሰበለት ግብ አይደርስም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment