Popular Posts

Sunday, January 29, 2017

ቅዱሳት መፅሃፍት


የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16-17
ለተሳካ የክርስትና ህይወት የእግዚአብሄር ቃል አስፈላጊነት ወሳኝ ነው፡፡ ካለ እግዚአብሄር ቃል እውነተኛ ስኬት የሚታሰብም አይደለም፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ እውቀት የሚገኝ ስኬት አስተማማኝና ዘለቄታዊ ስኬት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄር መንፈስ ያለበት መፅሃፍ
መፅሃፍ ቅዱስ የሰው ሃሳብ አይደለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ልብ ማሳያ መነፅር ነው፡፡
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10
እግዚአብሄር ሰውን ለክብሩ እንደ መፍጠሩ መጠን ሰው እግዚአብሄርን አስከብሮ የሚያልፈው በእግዚአብሄር መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ሊያስከብርና ሊያስደስት አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰው ልጅን የሚያስተዳደረው በራሱ መንገድ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ መረዳት የምንችለውና የቃልኪዳኑን ህግና ስርአት የምንረዳውና የምንከተለው ከመፅሃፍ ቅዱስ ነው፡፡
ለትምህርት ይጠቅማል
እውነተኛ ትምህርት የሚገኘው ከመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን እግዚአብሄርን ከመፍራት ጀምሮ እውነተኛ እወቀትን የምናገኘው በመፅሃፍ ቅዱስ ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን እውነተኛ እውቀትን ያካልፋል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በህይወት እጅግ ወሳኝ ስለሆኑ ስለ እግዚአብሄር ፣ ስለሰው ፣ ስለሰይጣን ፣ ስለምድር ፣ ስለአለም ፣ ስለሃጢያት ፣ ስለስኬት ፣ ስለዘላለማዊ ህይወት ስለመሳሰሉት ሁሉ ያስተምራል፡፡
ለተግሣጽ ይጠቅማል
እግዚአብሄር ማንንም አይፈራም፡፡ እግዚአብሄ የሚፈልገውን በመፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ ፅፎታል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ መልካም የሚያደርግን ሰው ያበረታታል እንዲሁም ክፉ የሚያደርግን ሰው ይገስፃል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የማያደርጉትን እንደልባቸው የሚኖሩትን ሰዎች ይገስፃል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ እንደመስታወት ተመስሏል፡፡ መስታወት ያለንበትን ሁኔታ እንዳለን የሚያሳየን  መፅሃፍ ቅዱስ መልካምና ክፉዋችንን በግልፅ በማሳየት ይገስፀናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ተመለሱ ፣ አይጠቅማችሁም ፣ ይጎዳችኋል ብሎ የተሳሳቱ ሰዎችን ይገስፃል፡፡
ልብንም ለማቅናት ይጠቅማል
ልብ በጣም ክፉና አስቸጋሪ በጥንቃቄና በትጋት ልንይዘው የሚገባው ነገር ነው፡፡ ልብ ከተጣመመ ሰው ይጣመማል ልብ ከቀና ሰው ይቀናል፡፡ ብዙ መፅሃፍት ስለስጋ ተናግረዋል ስለልብ ትክክለኛውን እውቀት የምናገኝበት እንደመፅፍ ቅዱስ ያለ መፅሃፍ ግን የለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የልባችንን ሁኔታ ፍንትው አድርጎ አሳይቶ ይመልሰናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ማንም ሳይንቲስት ሊደርስበት የማይችለውን ልባችንን ይደርሳል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ማንም ሊያደርገው የማይችለው መንፈስና ነፍስን እስኪለይ ድረስ ይወጋል የልብንም ስሜትና ሃሳብ ይመረምራል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
በጽድቅም ላለው ምክር
የመፅሃፍ ቅዱስን ምክር ተቀብሎ የሚሳሳት የለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በእውነት ይመክራል፡፡ የእግዚአብሄን የልብ ሃሳብ የምናገኘው በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ የመፅሃፍ ቅዱስ ምክር የማይረባውን እንዳንከተል የሚጠቅመውን አንድንይዝ ይመክራል፡፡ ከመፅሃፍ ቅዱስ ውጭ ፅድቅን ከፈለግን እንሳሳታለን፡፡
እግዚአብሄርን በሙላት የምንከተል ፍፁማን ሰዎች የሚያደርግን የቅዱሳት መፅሃፍት እውቀት ነው፡፡
ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15-17

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #ምክር #ቃልኪዳን #ተግሳፅ #ትምህርት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቅዱሳትመፅሃፍት  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የእግዚአብሄርመንፈስ #የእግዚአብሄርቃል

No comments:

Post a Comment