Popular Posts

Monday, November 7, 2016

በጌታ ደስ ይበላችሁ

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
በምድር ስንኖር በመጀመሪያ ጌታን በሚገባ እንዳንከተል ይህም ካልተቻለ በደስታ እንዳንከተለው የሚፈታተን ብዙ ነገር አለ፡፡
በአካባቢያችንም ያሉትን ነገሮች ብንመለከት ደስ እንዳንሰኝ የሚያደርጉ ነገሮች ለማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ ሰውን የሚያሳዝኑ ነገሮች ለማግኘት ብዙ መፈለግ አይጠይቅም፡፡ ፊት ከሰጠናቸው ደስ የማያሰኙ ነገሮች በአካባቢያችን ሞልተዋል፡፡
ጌታ በአንዳቸውም ነገሮች ደስ እንድንሰኝ አይጠብቅብንም፡፡ ሊያሳዝኑን ለሚመጡት ነገሮች ጀርባችንን ሰጥተን ደስ ልንሰኝበት የሚገባውን ጌታ ኢየሱስን ማየት ይገባናል፡፡ ደስታችንን ሊወስድ የሚመጣው ሊጥለን ፣ ሊያደክመን ፣ ሊያደናቅፈንና ሁሉንም እርግፍ አድርገን አንድንተው ለማድረግ ነው፡፡
ደስታው በተለያዩ ነገሮች ላይ የሆነ ሰው ለዚህ ጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡ ደስታው በሚሰማው ስሜት ላይ የሆነ ሰው በቀላሉ ከመንገዱ ሊደናቀፍ ይችላል፡፡ ክርስቲያን በሁኔታዎች ሳይሆን በጌታ ደስ መሰኘትን ሊለማመድ ይገባዋል፡፡ ደስታውን በጌታ በኢየሱስ ላይ ያደረገ ሰው ሊደናቀፍና ሊወድቅ አይችልም፡፡
የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡30-31
በጌታ ደስ የሚሰኝ ሰው ብቻ ከመድከም ይልቅ እየበረታ እየጨመረ በመሄድ በሙሉ ሃይል ወደ ፍፃሜው ይገሰግሳል፡፡ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ አላቸው። ነህምያ 8፡10
ማንም ሰው ደስ ለመሰኘት ምክኒያት ባይኖረው እኛ ህዝቦቹ በቂ ምክኒያት አለን፡፡ የሰማይና የምድር አምላክ አባት የሆነልን እኛ ምክኒያት ደስ ለመሰኘት በቂ ምክኒያት አለን፡፡
ማንም ደስ ባይለው እኛ ከሃጢያት ባርነት የዳንነው ደስ ይለናል፡፡ ማንም ደስ ባይለው እኛ የእግዚአብሄር ልጅ የሆንነው ደስ ይለናል፡፡ ማንም ደስ ለመሰኘት ምክኒያት ቢያጣ ስማችን በሰማይ የተፃፈና ወደየት እንደምንሄድ የምናውቅ እኛ ደስ ይለናል፡፡
እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? ዘዳግም 33፡29 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum...

No comments:

Post a Comment