Popular Posts

Sunday, November 13, 2016

ጥበብ ትጣራለች

ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች። ባሪያዎችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች፦ አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች፦ ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ። ምሳሌ 9፡1-6
ስለጥበብ ብዙ አይነት ትርጉም ሲሰጥ የቆየ ሲሆን እውነትም ጥበብን በአንድ አረፍተ ነገር መተርጎም አይቻልም፡፡
ጥበብ የእውቀት መተግበሪያ መንገድ ነው፡፡ ጥበብ ምን ማድረግ እንደሚገባን በማናውቅበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያሳየን የመረዳት ችሎታ ነው፡፡ በህይወታችሁ ሁሉ ነገር የተዘጋጋ የመሰላችሁ ነገር አለ? ለጥበብ መውጫ መንገድ አለ፡፡
ጥበብ ሃብታም ነች፡፡ ሰዎች ግን ካለ ጥበብ ምን ያህል ጎስቋላ እንደሚሆኑ ተመልክታ ጥበብ ትጮሃለች፡፡ ለምን በአላዋቂነት ትጠፋላችሁ? ለምን በህይወት አትኖሩም ? በህይወት መኖር እያለ ለምን በብክነት ትኖራላችሁ? እያለች ሁሉም ይሰማት ዘንድ በከፍተኛ ቦታ ላይ ትጮሀለች፡፡ የእርሱዋም ሳይበቃ በባሪያዎችዋ አማካኝነት ትጣራለች፡፡
ብዙ ጊዜ ብዙ ገንዘብ ብናገኝ ብዙ ፣ ንብረት ብናፈራ ፣ የተሻለ ቤት ውስጥ ብንኖር ፣ የተሻለ መኪና ብንነዳ ፣ ይበልጥ ታዋቂ ብንሆን ፣ ይበልጥ ሃይል ቢኖረን ህይወታችን የሚለወጥ ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ጥበብ ብርና ወርቅ የማይሰሩትን ነገሮች ትሰራለች፡፡
ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ምሳሌ 3፡13-14
ጥበብን ባገኘን ጊዜ ግን ያለን ነገር እንዳለ ሆኖ ካለምንም ተጨማሪ ወጭ ህይወትን መኖር እንችላለን፡፡ ጥበብ ሲኖረንና ሲበዛልን ደስተኛ ለመሆን የሆነ ጊዜን እንጠብቅም፡፡ጥበብ ሲኖረን ደስታችንንና እርካታችንን ለወደፊቱ አናስተላለፈውም፡፡ ጥበብ ከዛሬ ጀምረን ባለን ነገር መርካትና በህይወታችን እንድንደሰት ያስተምረናል፡፡
ከዚህ ጥቅስ በላይ ስለጥበብ ክብር የሚናገር ሃሳብ የለም፡፡ ስለጥበብ ክብር ብዙ ነገሮችን ይዘረዝርና እንዲህ በማለት ይደመድመዋል፡፡ እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። ምሳሌ 3፡19
ጥበብ ይህን ያህል በህይወት የተሞላች ከሆነች ጥበብ ታዲያ የሚገኘው እንዴት ነው ብለን እንጠይቃለን፡፡ ጥበብ በሁለት መንገድ ይገኛል፡፡ አንደኛ ጥበብ የተሞላውን የእግዚአብሄርን ቃል በማንበብና በመረዳት ጥበብ ይገኛል፡፡
ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15-17
ሁለተኛ ደግሞ ጥበብ ወደተሞላው ወደእግዚአብሄር በመፀለይ ጥበብ ይገኛል፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡5
ሶስተኛው ጥበብን የምናገኝበት መንገድ ደግሞ በጥበብ እየኖሩ ካሉት ከቀደሙት ምክርን በመቀበል ነው፡፡
ምክርን ስማ፥ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ። ምሳሌ 19፡20
ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፤ ምሳሌ 22፡17
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባለስልጣን #ጥበብ #ማስተዋል #መረዳት #ፀሎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment