Popular Posts

Friday, November 25, 2016

ካለ ንግግር ማመስገኛ መንገዶች

እግዚአብሄርን ማመስገን በአፍ እግዚአብሄር ሆይ አመሰግንሃልሁ ከማለት ያለፈ ነው፡፡
ለእግዚአብሄር መስእት ያመጡ ሰዎች በእግዚአብሄር ተገስፀዋል፡፡ የምስጋናን መስዋእት እንዲያመጡ እግዚአብሄር አዞዋል፡፡ በመኝሃፍ ቅዱስ ካለቃልና ካለንግግር ቀን ለቀን የእግዚአበሄርን ክብር እንደሚናገሩ ያስተምራል፡፡
ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። መዝሙር 19፡1-4
እግዚአብሄርን በቃላችን አመስግነን አንጠግብም፡፡ እግዚአብሄር ካደረገልን አንፃር የእግዚአብሄርን ውለታ በምንም አንከፍለውም፡፡ ከንግግር ውጭ ግን እግዚአብሄርን አመሰግንሃልሁ የምንልበት ሌሎች መንገዶች አሉ፡፡ ከንግግር ያለፈ በእያንዳንዱ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን እግዚአብሄርን ለማመስገን እድሉ ተሰጥቶናል፡፡ ካለንግግር እግዚአብሄርን የምናመሰግንበት ሰባቱ የህይወት ዘይቤዎች
  • · ለሰዎች በጎን ማድረግ
ከእግዚአብሄር መልካምነት የተቀበለ ሰው ሁሉ በተራው ለሰዎች መልካም በማድረግ እግዚአብሄርን በተዘዋዋሪም አመሰግናለሁ ይለዋል፡፡ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
  • · ሰዎችን ይቅር ማለት
እግዚአብሄር እርሱን ይቅር እንዳለው የተረዳና አመሰግናለሁ የሚል ሰው በተራው ይቅርታ የሚፈልግ ሰው ሲያገኝ ይቅር በማለት ካለንግግር እግዚአብሄርን በድርጊቱ ያመሰግናል፡፡ ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።ሉቃስ 12፡48 ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡32-33
  • · እግዚአብሄርን መታዘዘ
እግዚአብሄርን በንግግር ብቻ ማመስገን ፈፅሞ አያረካንም ፡፡ እግዚአብሄርን የምናመሰግንበት ሌላው መንገድ እግዚአብሄር እንዳስደሰተን እርሱን በመታዘዝ ማስደሰት ነው፡፡ በጌታ እንደረካንና ደስ እንደተሰኘን ማሳያው መንገድ ቃሉን በመታዘዝ በድርጊት ስናመሰግነው ነው፡፡ ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። ዮሃንስ 14፡23
  • · አለማጉረምረም
ህይወቱ እግዚአብሄርን የሚያመሰገን ሰው በንግግሩ እግዚአብሄርን ማመስገን ብቻ ሳይሆን በሚያልፍበት በማንኛውም መንገድ እግዚአብሄር ላይ አያጉረመርምም፡፡ የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25 ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ምሳሌ 17፡22
  • · ራስን ማዋረድና ወይም ትህትና
የሚያመሰግን ልብ ሁል ጊዜ ራሱን ለማዋረድ ዝግጁ ነው፡፡ የሚያመሰግን ልብ ያለው ሰው ሌሎች ሊሰሩት የማይፈቅዱትን ዝቅ ያለውን ነገር ያደረጋል፡፡ የምስጋና ህይወት ያለው ሰው ራሱን ከዝቅተኛ ሰዎች ጋር ሲያስተባብር ይታያል፡፡ እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ሮሜ 12፡16 (መደበኛ ትርጉም)
  • · በአስተሳሰብ ህይወታችን እግዚአብሄርን መፍራት
እግዚአብሄርን የምናመሰግን ከሆነ የእግዚአብሄር ያልሆኑትን ሃሳቦች እንጠየፋቸዋለን፡፡ የሚያመሰግን ልብ ካለን የእግዚአብሄርንና የእኛ ጠላት የሆነውን የሰይጣንን ሃሳብ አናስተናግድም፡፡ ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። መዝሙር 1፡1-2
  • እግዚአብሄርን መፈለግ
ለእግዚአብሄር በምስጋና የተሞላ ልብ ያለው ሰው ሁል ጊዜ እግዚአብሄርን በሁሉም የህይወት ክፍሉ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። መዝሙር 105፡1-4
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ምስጋና #እምነት #መደገፍ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

No comments:

Post a Comment