Popular Posts

Tuesday, November 22, 2016

መዳንህን እርግጠኛ ነህ?

መዳናችንን በእርግጠኝነት የምናውቅው ከስጋ ተለይተን ስንሞት ወይም ኢየሱስ ዳግም ተመልሶ ሲመጣ ነው ወይስ አሁን መዳናችንን ርግጠኛ መሆን እንችላለን የሚሉት ሃሳቦች ሰዎችን ያከራክራሉ፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ግን ስለመዳናችን ምን እንደሚል ማወቅ አሁን ስለመዳናችን ምንም ጥርጥር እንዳይኖረንና እንደዳነ ሰው የእግዚአብሄር ልጅነትን ስራ በምድር ላይ ሰርተን እንድናከብረው ያስችለናል፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በእኛ ምትክ ስለሞተና ስለተነሳ ኢየሱስ የሰራውን ስራ በእምነት ለእኔ ነው ብሎ ከመቀበል ወዲያ እኛ ለመዳናችን የምናደርገው ምንም ነገር የለም፡፡ የሚጠበቅንብን የደህንነትን ነፃ ስጦታ በእምነት መቀበል ነው፡፡
• ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን የሃጢያት እዳ ለእኔ ነው ብለን ከተቀበልን የዘላለም ህይወት አለን፡፡
ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 1ኛ ዮሐንስ 5፡12-13
• ኢየሱስ ከዘላለም ፍርድ ሊያድነን እንደ ተላከ የሚያምን ሰው ከሞት ወደ ህይወት ተሸጋግሯል ወደ ፍርድም አይመጣም፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። ዮሐንስ 5፡24
• ለእርሱ የሰጠነውን እንዳንሰናከል ማድረግ ይችላል፡፡ እንዲሁም ነውር የሌለን ሆነን በፊቱ እንድንቆም ማድረግ ይቻለዋል፡፡ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ይሁዳ 1፡24
• ለመዳን ወደ እርሱ ለመጣን ለሁላችን ሊማድልንና ፈፅሞ ሊያድነን ኢየሱስ በህይወት ይኖራል፡፡
ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ዕብራውያን 7፡25
• ኢየሱስን አዳኛችንና የህይወታችን ጌታ አድርገን ለተቀበልነው ሁሉ የዘላለም ህይወት ተሰጥቶናል፡፡ ከእግዚአብሄር እጅ ሊነጥቀን የሚችል ሃይል የለም፡፡
እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። ዮሐንስ 10፡28-29
• የአለም ህዝብ ተሰብስቦ አልዳንክም ቢለን እንኳን የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡16
• የመዳኛውን መንገድ ውስብስብ አይደለም፡፡ የዘላለም ህይወት የማግኛው መንገድ በኢየሱስ ማመን ነው፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። ዮሃንስ 6፡47
• ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፉ ከመሰከረ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልቡ ካመነ ሁሉ ይድናል፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10
ስለመዳንዎ አሁን እርግጠኛ መሆን ከፈለጉ ይህን ፀሎት ከልብዎ ይፀልዩ
እግዚአብሄር ሆይ ይህን የመዳኛ መንገድ በቃልህ ስለገለፅክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ ሃጢያተኛ እንደሆንኩ የሃጢያቴም ደሞዝ ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለያየት መሆኑን አውቄያለሁ፡፡ እኔ የዘላለምን ሞትን እንዳልሞት ኢየሱስ በእኔ ምትክ የሃጢያቴን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ እንደከፈለ አምናለሁ፡፡ እግዚአብሄርን ከሙታን እንዳስነሳው አምናለሁ፡፡ ኢየሱስ በሞት ላይ ጌታ እንደሆነ እንዲሁም በህይወቴ ላይ ጌታ እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡ ልጅ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አሜን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ደህንነት #ዘላለም #መዳን #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ኢየሱስ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment