Popular Posts

Friday, November 18, 2016

ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው 12 ምርጥ ስጦታዎች

ገንዘብን ልኩን አለማወቅ በህይወት እንድንሳሳት የሚያደርገን ሲሆን ህይወታችንን በሙላት እንዳንደሰትበት ያደርጋል፡፡ እንዲያውም የሰው ብስለት ማወቂያው አንዱ መንገድ ለገንዘብ ያለውን ግምት በመመልከት ነው፡፡ ሰው ለገንዘብ ያለውን ግምት ከተበላሸ ለሌሎች ለሁሉም ነገሮች ያለው ግምት ይበላሻል፡፡
ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው በህይወታችን በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ እንዲያውም በህይወት በጣም ውዶችና ወሳኞቹ ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው በስጦታ የምናገኛቸው ነገሮች ናቸው፡፡
  • · ገንዘብ የትኛውንም የእግዚአብሄርን ስጦታ ሊገዛ አይችልም
ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ሐዋርያት 8፡20
  • · የትኛውም ያህል ገንዘብ እውነተኛን ፍቅር ሊገዛ አይችልም
ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 8፡7
  • · ብዙ ገንዘብ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ጤናማ ግንኙነትን እግዚአብሄርን መፍራትን ሊገዛ አይችልም፡፡
እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። ምሳሌ 15፡16
  • · ገንዘብ ለህይወት እጅግ የሚያስፈልገንን ጥበብን ሊገዛ አይችልም፡፡ አእምሮን የሚከፍት ማስተዋልን የሚሰጥ እግዚአብሄር ነው፡፡
በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ምሳሌ 17፡16
  • · የእምነት መስዋእትነት እንጂ የገንዘብ ብዛት የእግዚአብሄርን ሞገስ አይገዛም፡፡
አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው። ማርቆስ 12፡43-44
  • እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ በፍፁም እድልና ጊዜን አያገናኝም
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
  • · እግዚአብሄር እንጂ የትኛውንም ገንዘብ የልብህምን መሻት ሊሰጥህ አይችልም፡፡
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መዝሙር 37፡4
  • · ገንዘብ ሰላምን ሊገዛ አይችልም
የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። ምሳሌ 15፡17
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃንስ 14፡27
  • · እግዚአብሄር እንጂ ገንዘብ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም ማድረግ አይችልም
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
  • · በገንዘብ ብዛት ህይወት አይለካም
የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ሉቃስ 12፡15
  • · ምንም አይነት ገንዘብ ስራን ሊሰራ ይችላል እንጂ ክንውንን ሊሰጥ አይችልም
እኔም መልሼ፦። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው። ነህምያ 2፡20
ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። ዘሌዋውያን 26፡4
  • · ምንም አይነት ገንዘብ ለሰው ነፍስ ቤዛ ሊከፈል አይችልም፡፡
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ማቴዎስ 16፡26
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ገንዘብ #ብር #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment