Popular Posts

Sunday, October 9, 2016

የምስጋና መስዋዕት

ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ። ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ መዝሙር 50፡7-14

ሰው ማንኛውንም መንፈሳዊ ተግባራት እያደረገ የእግዚአብሄርን አላማ ሊስተው ይችላል፡፡ሰው ወደ እግዚአብሄር እየፀለየ ፀሎቱ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር እየሰጠ ከእግዚአብሄር ጋር ሊተላለፍ ይችላል፡፡
እስራኤላዊያን ለእግዚአብሄር መስዋዕት ይሰዉ ነበር ፡፡ ነገር ግን መስዋእታቸው በግዴታ ላይ የተመሰረተ ይመስል ነበር፡፡ እግዚአብሄር የጠየቅከው ይህን ነው አይደል ያውልህ ብለው ወርውረው የሚሄዱ ነው የሚመስለው፡፡ እግዚአብሄር የፈለገውን ዋናውን የምስጋና ልብ ከእነርሱ ስላላገኘ ህዝቡ ከእግዚአብሄር ጋር ተላልፏል እግዚአብሄርም ይወቅሳቸዋል፡፡
እግዚአብሄርም መስዋእት እንዲያቀርቡለት ሲጠይቅ ምን እንደፈለገና ምን እንዳልፈለገ በዚህ ክፍል ሲናገራቸው እናያለን፡፡ እግዚአብሄር መስዋእትን ወይም አንድን ነገር እንድናደርግለት ሲፈልግ በምስጋና ልብ እንድናደርግለት ምስጋናን ፈልጎ እንጂ ነገሩን ፈልጎት አይደለም፡፡ እስራኤላዊያንን መስዋእት አምጡ ሲል ስጋ አምሮት ወይም ደም የሚጠጣ ሆኖ ሳይሆን መስዋእቱ ተሸክሞት የሚመጣውን ምስጋና ማየት ስለፈለገ ነው፡፡
እግዚአብሄር መስዋእት አድርጉልኝ ሲል ሃብትን መጨመር ፈልጎ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ባለጠጋ አምላክ ነው፡፡ ወይም ስንሰዋውና ስናጣው ብቻ ደስ ብሎት አይደለም፡፡
እግዚአብሄር ታዲያ ለምንድነው አንድ ነገርን እንድናደርግለት ወይም መስዋእት እንድናደርግለት የሚፈልገው ብንል ብልጠይቅ መልሱ እግዚአብሄር ምስጋናን ስለሚፈልግ ነው፡፡ በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሄር ከእኛ ሁል ጊዜ የምስጋናን ልብ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ስለሆነ እግዚአብሄር ኩሩ ስለሆነ በምስጋና ልብ ያላደረግነው ማንኛውም መስዋእት አይደሰትበትም አይመለከተውም፡፡ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ዘፍጥረት 4፡4
እኛ ደስ ደስ ሲለን ምስጋና በምስጋና እንደምናደርገው ትንሽ ሲጎድል ደግሞ ዝም እንደምንለው ሳይሆን እግዚአብሄር ሁልጊዜ ምስጋናችንን ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር ስጋን ባይበላም ምስጋናን ግን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ምስጋናን ሁሌ በመፈለጉ የተነሳ ሁኔታዎች ቢጨላልሙም ባይመስለንም እንኳን በእርሱ ታምነን ምስጋናን እንድንሰጠው ይጠብቃል፡፡ በደህናው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ጊዜም እግዚአብሄር ከሚታመኑት የምስጋናን መስዋዕትን ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር የሚጠማውና የሚራበው ምስጋና ማጉረምረምረም ሲያሰኘን ሁሉ ነገር እግዚአብሄርን እንዳናመሰግን ሲያስፈራራን የዛን ጊዜ የምናመሰግነውን ነው፡፡
በተለይ ነገሮች ሁሉ አይሆንም አይሳካም አይከናወንም ሲሉን እግዚአብሄርን የምናመሰግነው ምስጋና እንደ ሽቱ በእግዚአብሄር ዘንድ የተወደደ ነው፡፡ ነፍሳችን ማጉረምረም ሲያምራት እምቢ ብለን የምንሰዋው ምስጋና ነው የምስጋና መስዋእት የሚባለው፡፡
ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። መዝሙር 43፡5
መስዋእታችን የልባችንን ምስጋና እንዲሸከም ስለተፈለገ ነው እንጂ እግዚአብሄር መስዋእት የምናደርገው ነገር ፈልጎትና ቸግሮት አይደለም፡፡ እስራኤላዊያን የልባቸውን ምስጋና የመወርወር ያህል ጥለው ይሄዱ ስለነበረ እግዚአብሄር ምስጋናን የተሸከመ መስዋዕትን ነው የምፈልገው እያለ ሲወቅሳቸው እንመለከታለን፡፡ የመስዋእቱ አላማ የተሸከመው ምስጋና እንጂ ስጋው አይደለም እያለ ነው፡፡
ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #ሞት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment