Popular Posts

Friday, October 7, 2016

የህይወት ሚዛን

ህይወት ታላቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ህይወትን ትልቅ ሃላፊነት ያደረገው ምክኒያቱ ሚዛኑን ጠብቀን በጥንቃቄ የምንኖረው ስለሆነ ነው፡፡
ለምሳሌ በተለይ በዚህ ዘመን እውቀት ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በጥበብ አመዛዝኖ ለሌሎች በሚጠቅም ሁኔታ እውቀትን መተግበር ሚዛናዊነትን ይጠይቃል፡፡
ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ ቆላስይስ 1፡9
ስለዚህ ነው ህይወት የሚዛናዊነት ጉዞ ነው የሚባለው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ ማለቱ በአንተና በሌላው መካከል ያለውን ሚዛናዊነት ጠብቅ ማለቱ ነው፡፡ ታዲያ ራስ ወዳድነት የሚባለው ይህ ሚዛን ሲጣስ ሲሆን ህይወት በአንድ ወገን ብቻ ሲያጋድል ህይወት ሚዛኑንና ትርጉሙን ያጣል፡፡
እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ሉቃስ 10፡27
መፅሃፍ ቅዱስ ስለኑሮ እንኳን ሲናገር በመጠኑ ኑሩ ንቁም ይላል፡፡ ያ ማለት ለህይወታችን የሚያስፈልገውን መጠቀምና ለህይወት በሚያስፈልገን ነገር ብቻ መወሰን እንዳለብን እያስገነዘበ ሲሆን ህይወትን ከመሰረታዊ ፍላጎት በላይ ሚዛኑን አለማሳለፍ ማለት ነው፡፡ ምንም መልካም ነገር ከመጠን ሲያልፍ ጎጂ ይሆናል፡፡ የኑሮዋችንን ሚዛናዊነቱን ስንጠብቅ ብቻ ነው ከመጠን የማናልፈው ለሌሎችም በረከት መሆን የምንችለው፡፡
በመጠኑ ኑሩ ንቁም፥ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያጋሳ አንበሳ ይዞራልና፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8
መፅሃፍ ቅዱስ ተቆጡ ብሎ ይፈቅድልንና ነገር ግን ቁጣችን ከመጠኑ እንዳያልፍ ሚዛኑን እንድንጠብቅ ያስተምረናል፡፡ ቁጣችን ከቁጥጥር ወጥቶ ሃጢያት እስኪያሰራን መሄድ እንደሌለበት መፅሃፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል፡፡ የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ አይሰራም በማለት ቁጣ ሚዛናዊ መሆን እንዳለበት ያሳየናል፡፡ ምክኒያቱም ቁጣ ሊሰራ የሚችለውም ሊሰራ የማይችለውም ነገር እንዳለ እያስተማረ ሚዛኑን እንዳንስት ያሳስበናል፡፡
ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡26-27
እውነትን ስንናገር እንኳን እውነት ክቡር ሆኖ ሳለ በፍቅር እንድናደርገው ያስተምራል፡፡ እውነትና ምህረት ሚዛኑን ከሳተ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያስተምረናል፡፡ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ኤፌሶን 4፡15
ኢየሱስ ይመጣል ነገር ግን ኢየሱስ ስለሚመጣና ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥም፡፡ ኢየሱስ ይመጣል ወንጌልን በትጋት እንሰራለን፡፡ ማራናታ ኢየሱስ ሆይ ና እንላለን፡፡ ከመምጣቱ በፊት በትጋት ወንጌልን ለመስራተ እንሮጣለን፡፡
ለቤተስብ ብለን ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አለ ፡፡ ለአገልግሎት ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አለ፡፡ ለግል መንፈሳዊ ህይወታቸን ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አለ፡፡ ሌሎችን ለማገልገል ቅድሚያ የምንሰጥበት ጊዜ አለ፡፡ ይህን የህይወትን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ሁሉንም በልክ አድርግ ያለው የሃዋሪያው ጳውሎስ ምክር በጣም ወሳኝ ነው፡፡
አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። ሉቃስ 10፡5
ሚዛኑን የሚጠብቅ ሰው አንዴ ሚዛኔን ጠብቄያለሁ አሁን መጠንቀቅ የለብኝም እንደማይል በህይወትም ሚዛን መጠበቅ የሁልጊዜ ሃላፊነት እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ በየትኛውም ፅንፍ ሳይያዙ በግራም ጉድጓድ ሳይገቡ በቀኝም ጉድጓድ ሳይገቡ በመሃል መንገድ መጓዝ ጤናና ብስለት ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ሚዛን #በመጠን #ራእይ #መዳን #እምነት #በልክ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment