Popular Posts

Thursday, October 13, 2016

ብልቶች

በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ሮሜ 12፡5-8

የሰው አካል ክፍሎች በአንድነትና በህብረት ተግተው ለአካሉ መልካምነት እንደሚሰሩ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖችም ብዙ አይነት የአገልግሎት ጥሪዎችና ስጦታዎችም ቢኖሩን ሁላችን ለአንድ ግብ እንደምንሰራ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
በአንድ አካል ላይ ያለን የተለያዩ ብልቶች ብንሆንም ሁላችንም ለአንድ አካል የምንሰራ የአካል ክፍሎች ነን፡፡
ለአንድ አላማ ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ስራ መስራት የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ሰዎች መሆን የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት አገልግሎት ሊኖረን አይገባም፡፡ የእምነት ደረጃችን እኩል መሆን የለበትም ለአንድ መንግስት ለመስራት፡፡ ሁላችንም አንድ አይነት ስራ ከሰራን ውበትም ውጤትምን አይኖረውም፡፡
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡17
ሁላችንም ስራችን የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም ለአንድ ግብ መስራት እንችላለን፡፡
የሁላችንም ስራ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም እጅግ አስፈላጊዎች ነን፡፡ የማያስፈልግ የአካል ብልት የለም፡፡ እንዲያውም ደካማና የማያስፈልጉ የሚመስሉት እነርሱ ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22
ማንም ከማንም ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ነው እንጂ እንዲፎካከር አልተፈቀደም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲመካ በፍፁም አልተፈቀደም፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
የአንድ አካል ብልቶች ሆናልና አንድ አካል ሲከብር ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይከብራሉ አንድ አካል ሲሰቃይ ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይሰቃያሉ፡፡
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26
እንዲያውም ደካማ ለሚመስለው የአካል ብልት ይበልጥ ክብር ይጨመርለታል፡፡ ፀጋም የሚበዛለት ለደካማው ብልት ነው፡፡
ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡23
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡27
ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። ኤፌሶን 4፡15-16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #አካል #ብልት #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

No comments:

Post a Comment