Popular Posts

Wednesday, October 5, 2016

ቃሉን መተግበር

እግዚአብሄርን ማስደሰት የመጀመሪያ ፍላጎታችን ስለሆነ ልክ የእግዚአብሄርን ቃል ስናገኝ በራሳችን ልንፈፅመው እንሞክራለን፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ቃል አገኘነው ማለት በራሳችን እናደርገዋለን ማለት አይደለም፡፡
ስለዚህ ነው በህይወታችን ስለ እግዚአብሄር ቃል ስናስብ ከብዛቱ የተነሳ እንዴት እንደምንተገብረው ግራ ይገባናል፡፡ በህይወቴ ከተማርኩት የእግዚአብሄርን ቃል ለመተግበር ከሚረዱ ነገሮች ጥቂቱን ላካፍላችሁ፡-
የእግዚአብሄር ቃል እንድትገብሩ እናንተ ከምትፈልጉት በላይ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል መተግበር ከእግዚአብሄር ጋር አብራችሁ የምታደርጉት እንጂ ብቻችሁን ስትሞክሩ እግዚአብሄር እንደታዛቢ የሚያያችሁ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቃሉን በመፈፀም ሂደት እግዚአብሄር ሙሉ በሙሉ አብሮን መስራት ይፈልጋል፡፡
የእግዚአብሄርን ቃል ለመፈፀም መንፈስ ቅዱስ ሊያስታውሰን ሁሌ ከእኛ ጋር አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጌታ ሲናገረኝ መንፈስ ቅዱስ ይህንን እንግዲህ በጊዜው አሳስበኝ ብዬ ለእርዳታ ልቤን አነሳለሁ፡፡
አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ዮሃንስ 14፡26
ምክኒያቱም መንፈስ ቅዱስ ራሱ ነው ያ ማለት ይህ ማለት ነው ብሎ የሚያስታውሰንና በተግባር የሚያሳየን፡፡
ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። ሐዋርያት 2፡16
የእግዚአብሄርን ቃል ማወቃችን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምንፈፅመው እግዚአብሄር ጥበብን ሊሰጠን ይገባል፡፡ ምን እንደምናደርግ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምናደረግ የእግዚአብሄር መንፈስ ሊያሳየን በዝርዝር ጉዳዮች ጥበብን ሊሰጠን ይገባል፡፡
የእግዚአብሄርን ቃል መተግበር የምንችለው በራሳችን ጉልበት መታመን ስናቆምና በእርሱ መንፈስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ስንደገፍ ብቻ ነው፡፡ በራሳችን ለመተግበር ከሞከርን አንችልም፡፡
የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። ሮሜ 7፡15
የእግዚአብሄርን ቃል ለመፈፀም በእግዚአብሄር ቃል ከባቢ ውስጥ መሆን ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ማሰብና ማሰላሰል ቃሉን እንድንተገብረው ተግባራዊ መረዳት ይሰጠናል እንዲሁም ሃይልን ያስታጥቀናል፡፡ ቃሉን ስናሰላስል ይበልጥ ብርሃን ይሰጠናል ዝርዝር አፈፃፀሙን ያሳየናል፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ 1፡8
በእርግጥ በተረዳነው በእግዚአብሄር ቃል ጀምረን ቃሉን ለማድረግ መነሳት አለብን፡፡ አንዳንዴ የተፃፈውን ቃል ሁሉ ለማድረግ ስናስብ ይጨንቀናል እንዲያውም እግዚአብሄር የማይቻል ነገር እንዳዘዘን ሁሉ ሊሰማን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር ያዘዘን ሁሉ የሚቻል ነገር ነው ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ቃል መፈፀም ያለብን በእርግጥ ለተረዳነው ቅድሚያ በመስጠት መሆን አለበት፡፡ ከሁላችንም እኩል አይጠበቅምንም ከእያንዳንዳችን ግን እንደ መረዳታችን መጠን ይጠበቅብናል፡፡
የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48
ህፃን በወተት እንደሚያድግና ለጠንካራ ምግብ እንደሚዘጋጅ ሁሉ ከተረዳነው ከምናውቅው ጀምረን የእግዚአብሄርን ቃል ስንፈፅም ቃሉን መፈፀማችን መንፈሳዊ ጡንቻችንን ስለሚያጠነክረው እግዚአብሄር ሌሎች ቃሎችን እንድንታዘዛቸው ያሳየናል፡፡
የእግዚአብሄርን ቃል ስንፈፅም እግዚአብሄርን ማመስገን ይኖርብናል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ

No comments:

Post a Comment