Popular Posts

Sunday, October 30, 2016

የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ

ዶክተር አሳየኸኝ በርሄ ስለጋብቻ ሲያስተምሩ የወደፊት የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ለሚደረግ ፀሎት ሰባት ጠቃሚ መርሆዎችን ተናግረዋል፡፡ ይህን ከእናንተ ጋር ለመካፈል ወደድኩ፡፡
ይህ የፀሎትና የእግዚአብሄርን ፈቃድ መለያ መመሪያ ማንም ሰው ለሌሎች የህይወት ክፍሎች ለመወሰንና ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግና የሚጠቅሙ የፀሎት መርሆዎች ናቸው፡፡
1. ስትፀልይ ወስነህ አትፀልይ፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ስትፀልይ የምታደርገውን አውቀህ እግዚአብሄር እንዲያፀናልህ ብቻ አትፈልግ፡፡ እግዚአብሄር በህይወትህ በእያንዳንዱ ደረጃ መካተት ይፈልጋል፡፡ የምትፈልገውን መርጠህ ጨርሰህ እግዚአብሄር ማህተም ብቻ እንዲያደርግልህ አትፈልግ፡፡ ስትፀልይ ገለልተኛ ኒውትራል ሆነህ ፀልይ፡፡ አስቀድመህ ወስነህ ከፀለይክ እግዚአብሄር ቢናገርህም መስማት ያቅትሃል፡፡
ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ማቴዎስ 26፡39
2. የመንፈስ ቅዱስን መቃተት ጠብቅ እግዚአብሄር በምርጫህ ውስጥ መካተቱን የምታውቀው ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስ መቃተትን ስታገኝ ነው፡፡ ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘትህን የእግዚአብሄር በመለየት ፀሎትህ እንደተካተተ እርግጠኛ ሁን፡፡ ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስን መቃተት እሰኪሰማህ ድረስ ፀልይ፡፡
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ሮሜ 8፡26
3. መነሻ ሃሳብህን ሞቲቭህን ፈትሽ ለትዳር ጓደኛ ምርጫ ስትፀልይ የውስጥ ሃሳብህን ወይም ሞቲቭህን መዝን፡፡ ምርጫህን ልትመርጥ የቻልከው ለምን እንደሆነ ራስህን በቅንነት ጠይቅ፡፡ ሰው በስጋ ሃሳብ ተነስቶ ሊፀልይ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር የሚመልሰው ፀሎት ግን ሞቲቩን ለማጥራት ራሱን የሚፈትሽና ራሱን የሚያስተካክል ሰው ፀሎት ነው፡፡
የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል። ምሳሌ 16፡2
4. ካንተ በመንፈሳዊ ነገር ከበሰሉ ሰዎች ምክርን ጠይቅ፡፡ ይህ ማለት እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያትን ጠይቅ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ምርጫን እንዴት ልትመርጥ እንደምትችል የምርጫህን መመዘኛዎች እንደ እግዚአብሄር ቃል ሊያስተካክሉ የሚችሉ በቃሉ የበሰሉ ለህይወትህ እውነተኛ ሸክም ያላቸውን ሰዎች ምክርን ተቀበል፡፡
በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው። ምሳሌ 24፡6
5. እግዚአብሄር ማረጋገጫን እንኪሰጥህ ጠብቅ፡፡ እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በተለያዩ መንገዶች ቃሉን ያፀናል፡፡ ስለዚህ በአንድ ሃሳብና በአንድ ምሪት ብቻ ከመሄድ ማረጋገጫዎችን ጠብቅ፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡16
6. ምርጫን ስታደርግ የእግዚአብሄር ሰላም በልብህ እንዳለ እርግጠኛ ሁን፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ ያለበት ነገር ሁሉ በውጭህ ረብሻ ቢሆንም በውስጥ ሰላም ይኖርሃል፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበትን ነገር ለማድረግ ስታስብ በአእምሮህ እንኳን ረብሻ ቢኖርም በልብህ ግን ሰላም ይኖራል፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15
7. ሌላው የእግዚአብሄር ፈቃድ ማረጋገጫው እግዚአብሄር በሮችን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር ለፈቃዱ የሚያስፈልጉትን አቅርቦቶች ይሰጣል፡፡ የተሳኩ ነገሮች ሁሉ የእግዚአብሄር ፈቃድ ናቸው ባንልም የእግዚአብሄር እጅ ያለበት ግን ይሳካል ነገሮችም ይሰካካሉ፡፡
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 23፡1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #ስለሁሉሞተ

No comments:

Post a Comment