Popular Posts

Sunday, September 11, 2016

የስኬት ቁልፍ

ህይወትን ይኖሩታል እንጂ በአንድና በሁለት አረፍተ ነገር ወይም በብዙ ፅሁፎች ሊገልፁት አይችሉም፡፡ ህይወት ሁሉ ነገር ፍንትው ብሎ የሚታይበት ነገር ሳይሆን ሚስጢራዊነት ያለው አሰራሩን መረዳት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ የህይወት ቁልፍ ሚስጢር ነው፡፡ ሰው እንዴት እንደሚሳካለትና እንደሚከናወንለት ለማወቅ ብዙ ሰዎች ካለማቋረጥ ይመራመራሉ፡፡ የተለያዩ የስኬት መንገዶች ናቸው የሚሏቸውን ሲያስቀምጡ ይታያል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ስኬት እንዴት እንደሚመጣ የክንውንን ቁልፍ ለማወቅ እጅግ የደከመውን ጠቢቡን ሰለሞን እንመለከታለን፡፡ ንጉስ ሰለሞን እነዚህን የሚላቸውን ሃያልነት ባለጠግነትና ጥበበኝነት በተግባር ደርሶባቸው እንደሚሰሩና እንደማይሰሩ በህይወቱ የፈተናቸው ነገሮች ናቸው፡፡
ጠቢቡና ሰለሞን ተመራምሮ ተመራምሮ የደረሰበትን ሚስጢር ይነግረናል፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን የስኬት ቁልፍ አብዛኛው ሰው ከሚያስበው የተለየ መሆኑን እሱም ሃሳቡን እንደለወጠ እኔም ተመለስኩ ብሎ ምን እንደተረዳ ያስረዳናል፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
ተመልከቱ እግዚአብሄር አይሆንም ካለ የሩጫ ድል ለፈጣን አይሆንም፡፡ስንቱ ፈጣን ሯጭ የሂሳብ ባለሞያ ሆኗል፡፡ ፈጣኑ ሯጭ ስንት ጊዜ ተስፋ ቆርጦ እግዚአብሄር በሰው ተጠቅሞ አበረታቶታል ከወደቀበት እንደገና አንስቶታል፡፡
ስንቱ ሃያል እዚህ ግባ በማይባል ደካማ ሰው ተሸንፏል፡፡ ስንቱ ደካማ ሃያሉን ሰው አዋርዶታል፡፡ ዳዊትን ሃያሉን ጎሊያድን ሲያሸንፍ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።1ኛ ሳሙኤል 17፡47
እግዚአብሄር ካልሰጠ ባለጠግነት በቅልጥፍና አይመጣም፡፡ ስንቱ በትንሽ ነገር ምክኒያት ሊይዘው ካለው የባለጠግነት ደረጃ ወድቆዋል ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ሳያስበው ባለጠግነት ወድቆበታል፡፡
ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። 1ኛ ሳሙኤል 2፡8
እግዚአብሄር ይሁን ካላለ ሰው አዋቂነቱ ብቻ ሞገስን አይሰጠውም፡፡ የስንት አስተዋዮች ማስተዋል ተጥሏል፡፡ ብዙ የማይጠበቅበት ሰው ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በዚያም ወራት የመከራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ነበረች፤ የአኪጦፌልም ምክር ሁሉ ከዳዊትና ከአቤሴሎም ጋር እንዲህ ነበረች። 2ኛ ሳሙኤል 16፡23
አቤሴሎምና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ። የአርካዊው የኩሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይሻላል አሉ። እግዚአብሔርም በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ።2ኛ ሳሙኤል 17፡14
ሁሉን የሚያሰካካውና የሚያገናኘው የጊዜና የእድል ባለቤቱ እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡እነዚህን ፈላጊና ተፈላጊ የሚያገናኘው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
የስኬት ቁልፉ ያለው ባለጠግነትም ሃያልነትም ጠቢብነትም ጋር ሳይሆን የክንውን ቁልፉ ያለው እግዚአብሄር ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አይኖቻችን ወደአንተ ናቸው፡፡ በሃይላችን በጥበባችን በሃብታችን አንታመንም፡፡ በአንተ ብቻ እንታመናለን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ስኬት #ባለጠጋ #ጠቢባን #ሃያላን #ሞገስ #ክንውን #በረከት #ቃል #ፀሎት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment