Popular Posts

Friday, September 9, 2016

በፈቃዱ ውስጥ እንዳለው በምን አውቃለው?

በእየሱስ የመስቀል ስራ ከእግዚአብሄ ጋር ከታረቅን በኋላ የመጀመሪያው በህይወታችን የምንፈልገው ነገር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ነው፡፡ በህይወታችን የምንጠላውና የማንፈልገው ነገር ደግሞ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጭ መገኘትን ነው፡፡
አብዛኛው ክርስትያን በህይወቱ የሚፈልገው ዋና ነገር ምን እንደሆነ ቢጠየቅ የሚመልሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማድረግና እግዚአብሄርን በህይወቱ ማክበር ነው፡፡
ግን አንዴት ነው የእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ መሆኔንና አለመሆኔን የማውቀው የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ መሆናችንን ለማወቅ የሚረዱ ሰባት ነጥቦች፡፡
1. የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ከምንጠማው በላይ እግዚአብሄር ፈቃዱን እንድናደርግ ይፈልጋል፡፡ እንዲያውም ሲጀመር የፈጠረን ፈቃዱን እንድናደርግ ለክብሩ ነው ፡፡ ፈቃዱን አንድንረዳና እንድናደርግ ሙሉ ለሙሉ አብሮን ይሰራል፡፡
በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳይያስ 43፡7
2. የእግዚአብሄርን ፈቃድ መረዳት ለሁላችን የተሰጠ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድን መረዳት ለጥቂት ሰዎች የተሰጠ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አማኝ የተሰጠ ዕድል ነው፡፡ የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። ዮሃንስ 10፡4-5
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ዮሃንስ 10፡14
3. የእግዚአብሄር ፈቃድ ውስብስብና ለመረዳት የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 1ኛ ዮሐንስ 5፡3
4. የእግዚአብሄርን ፈቃድ የምንረዳው ከተናጋሪው ችሎታ እንጂ ከሰሚው ችሎታ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ፈቃዱን የሚያሳውቀን በመስማት ደረጃችን ወርዶ በሚገባን መንገድ ነው፡፡ ፈቃዱን ለማወቅ እስከፈለግን ድረስ እስኪገባን ድረስ ይናገረናል፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ዮሃንስ 7፡17
5. በጣም አስደናቂ በሆነ በደመናና በታላቅ ድምፅ አልተናገረንም ማለት እየመራን አይደለም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አብዛኛውን ጊዜ በልባችን በለሆሳስ ነው የሚናገረን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሄርን ምሪት እንዲሁ እንረዳዋለን እንጂ ማስረዳት ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሲናገር ግን እናውቀዋለን፡፡
እርሱም፦ ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። 1ኛ ነገስት 19፡11-12
6. በአጠቃላይ እግዚአብሄር በእኛ ደስተኛ ነው፡፡ ደስተኛ ካልሆነ ይናገረናል፡፡ እግዚአብሄር ተበሳጭቶብን ኖሮ ኖሮ ድንገት ሲደሰትብን አይደለም የሚናገረን፡፡ እግዚአብሄር በእኛ በደረስንበት ደረጃ ባለንበት ሁኔታ ደስተኛ ነው፡፡ ያልተደሰተበት ነገር ካለ ያሳየናል፡፡ እኛ ራሳችንን ከምንረዳው በላይ እርሱ እኛን ይረዳናል፡፡
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ሮሜ 8:1
7. ፈቃዱን ለማድርግ መፈለግንና መነሳሳትን በምህረቱ የሚሰጠን አግዚአብሄር ነው፡፡ ስለ መልካምነቱ እንዲሁ ማድረግን የሚሰራው እርሱ ራሱ ነው፡፡
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ፊልጵስዩስ 2፡10

No comments:

Post a Comment