Popular Posts

Sunday, September 18, 2016

ድንበር ይከበር!

በክርስትና ህይወት ዘመኔ ድንበርን እንደማለፍና ልክን እንዳለማወቅ የክርስቲያንን ሰላም የሚረብሽ ነገር አላየሁም፡፡ ክርስትና የእግዚአብሄርና የሰው ድርሻ ያለበት ስራ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራው ነገር አለ፡፡ ሰው የሚሰራው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር የማይሰራው ነገር አለ፡፡ ሰው የማይሰራው ነገር ደግሞ አለ፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር አብረን የምንሰራ ነንና፡፡ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ህንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሰራ ነንና፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡9
ሰው ይህንን ሲረዳ መስራት ያለበትን ሰርቶ እርፍ ይላል፡፡ ሰው ግን ይህንን የስራ ክፍፍል ካልተረዳ የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት ሲሞክር ተስፋ ይቆርጣል ሰላሙንም ያጣል፡፡ ሰው ድርሻዬን ተወጥቻለሁ የሚልበት ደረጃ ከሌለ ጭንቀት ውስጥ ይገባል፡፡ ክርስትናውን ሊደሰትበት ያቅተዋል፡፡
  • ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከተረዳና ካደረገው በኋላ የእግዚአብሄርን ድርሻ መተው አለበት፡፡ የተስፋ ቃሉን መስጠት የእግዚአብሄር ስራ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካደረገ በኋላ ማረፍ ዘና ማለት አለበት፡፡ እግዚአብሄር ብቻ የሚፈፅመውን የተስፋ ቃሉን በራሱ ሊፈፅም መታገል የለበትም፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
  • ሰው የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ከፈለገ እግዚአብሄር ስለሚፈፅመው መብልና ልብስ መጨነቅ የለበትም፡፡ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ለክርስቲያን በቂ ሃላፊነት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን በመፈለግ ብቻ እርፍ ሊልና ደስ ሊሰኝ ይገባዋል፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
  • በህይወታችን ፅድቅን መራብና መጠማታችን በቂ ነው፡፡ የሚያጠግበው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ተርበንም እራሳችንን ለማጥገብም ከሞከርን ድንበር እያለፍን ስለሆነ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ማቴዎስ 5፡6
  • በመንፈሳዊ ህይወታችን ለማደግ ማድረግ የምንችለው ውስን ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ማጥናትና መታዘዝ ፣ ወደእግዚአብሄር መፀለይ ከቅዱሳን ጋር ህብረትን ማድረግ የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ሰው ግን ይህንን ካደረገ በኋላ ራሱን ሊያሳድግ በሚሞክረው ሙከራ ይረበሻል፡፡ የሚያሳድግ እግዚአብሄር ብቻ ነውና፡፡
እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡7
  • ሰው የዛሬን ሃላፊነቱን ከተወጣ ማረፍ ደስ መሰኘት የሰላም እንቅልፉን መተኛት አለበት፡፡ ሰው ግን የነገን ሃላፊነት ዛሬ ሊሰራው ሲሞክር ሰላሙን ያጣል፡፡ ህይወቱን ደስ ሊሰኝበት ያቅተዋል፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34
  • ሰው ክፋትን ሲሰራብን መቆጣት የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በቀልና ብድራትን መመለስ የእኛ ሃላፊነት አይደለም፡፡ ተቆጥተንም ብድራትንም ለመመለስ ስንሞክር ካለአቅማችን የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት እየሞከርን ነውና አይሳካልንም፡፡ እግዚአብሄርንም አይደሰትብንም፡፡ ነገር ግን ድርሻችንን አውቀን ለቁጣው ስፍራ መስጠት አለብን፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
  • ለክርስቲያን በኑሮም ሆነ በቃል ወንጌልን መስበክ የእለት ተእለት ስራው ነው፡፡ ነገር ግን ሰውን መለወጥ የሰው ስራ አይደለም፡፡ የሰው የወንጌል አገልግሎቱ የሚለካው በሚኖረው የህይወት ምስክርነትና በቃል የሚመሰክረው ምስክርነት ትጋት ብቻ እንጂ ጌታን በተቀበሉስ ሰዎች ብዛት አይደለም፡፡ የሚወቅስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
እርሱም (መንፈስ ቅዱስ) መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ዮሃንስ 16፡8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ንጉስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment