Popular Posts

Sunday, September 18, 2016

ቀዳሚው ጥሪ

ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። ኤፌሶን 6፡5-9
ክርስትያን ስንሆን ጥሪያችን ሁሉ ሰማያዊ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ጥሪው በመጀመሪያ የክህነት አገልግሎት ነው፡፡ ዋናው ጥሪው ክህንነት ነው፡፡ ክርስቲያን ካህን ነጋዴ ፣ ካህን ሃኪም ፣ ካህን አስተማሪ ፣ ካህን ሹፌር ፣ ካህን ፀሃፊ ፣ ካህን ወታደር እንዲሆን ነው የተጠራው፡፡
ክርስቲያን ነጋዴ መሆኑን ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ አስተማሪ ማስተማሩን ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ ሃኪም ህክምናውንም ቢያቆምም ክህንነቱን አያቆምም፡፡ ካህን ማለት በእግዚአብሄርና በሰው መካከል የሚቆምና እግዚአብሄርን በማገልገል ሰውን የሚያገለግል ማለት ነው፡፡ ካህን እግዚአብሄርን ወክሎ በሰው ፊት ይቆማል፡፡ ካህን ሰውን ወክሎ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል፡፡ ካህን ስለሰው ለእግዚአብሄር የሚናገር እንዲሁም ስለ እግዚአብሄር ለሰው የሚናገርና የሚመሰክር ነው፡፡
በቤተሰብ ውስጥ ያለ ልጅ ልጅ ስለሆነ ብቻ አባቱ እንደሚንከባከበውና የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያሟላለት ልጅ ስለሆንን ብቻ ነው እግዚአብሄር የሚንከባከበን፡፡ እግዚአብሄር ስራን የሚሰጠን እኛን ለመንከባከብ ቸግሮት አይደለም፡፡ ስራን የሰጠን በዋነኝነት የክህንነት ስራችንን እንድንፈፅምበት ነው፡፡ እግዚአብሄር በየሙያ ዘርፉ የበተነን በእግዚአብሄር ልጅነት ባህሪ ተፅኖ እንድናመጣ ነው፡፡
እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 5፡14
እንደክርስቲያን ለአምልኮ በአንድ ላይ እንሰበሰባለን ከዚያም የመንፈሳዊ ህይወት ደረጃና እውነተኛውን መንገድ ለማሳየት ሰው ወደሚገኝበት ቦታ ሁሉ ወደ ክህንነት አገልግሎታችን እንበታተናለን፡፡
እግዚአብሄር ለምድር ጨውና የአለም ብርሃን እንድንሆን ነው እግረመንገዳችንን ስራን እንድንሰራ የፈለገው፡፡
እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ማቴዎስ 5፡15
ስራ የሰጠን ሰዎች መልካም ስራችንን አይትተው የሰማዩ አባታችንን እንዲያከብሩ የእርሱን ክብር ለሰዎች እንድናንፀባርቅ ነው፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
ለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ በገንዘብ የተገዙ ክርስትያን ባሪያዎችን እንኳን የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው በማለት ቀዳሚውና ዋነኛ ጥሪያቸው ክህንነት እንደሆነ የሚያስተምረው፡፡ ጥሪያችሁ ሰማያዊ ነው፡፡ የጠራችሁ እግዚአብሄር ነው፡፡ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው፡፡
ስራችሁ ሁሉ በቀዳሚነት አገልግሎት እንጂ የገንዘብ ማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ ገንዘብ የምታገኙት የክህነት አገልግሎታችሁን ስትሰሩ እግረመንገዳችሁን ስራውን ስለምትሰሩት ነው፡፡
ስለዚህ አገልግሎታችሁን ስትወጡ ለክህንነት አገልግሎት የጠራችሁን ጌታን እንጂ የምድር ጌቶቻችሁን እያያችሁ መሆን የለበትም፡፡ የምድር ጌታችሁ በማያይበት ጊዜ ሁሉ ለክህንነት የጠራችሁ ስለሚያያችሁ ለታይታ ብቻ አትስሩ፡፡ ስትሰሩ ለሰማዩ ጌታ እንደሚገባ በሙሉ ልባችሁ በትጋት ስሩ፡፡
ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ቆላስይስ 3፡22-23
የመጀመሪያ ጥሪያችሁ ሰማያዊ ቀዳሚው ሙያችሁ ክህንነት ስለሆነ ቀዳሚው ቀጣሪያችሁና ከፋያችሁ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ለምድር ጌቶቻችሁ ከልባችሁ ስትታዘዙ ስለክፍያ በፍፁም አታስቡ፡፡
ከፋያችሁ የቀጠራችሁ ለክህነት የጠራችሁ እርሱ ክርስቶስ ነው ፡፡
ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም። ቆላስይስ 3፡24-25
እግዚአብሄር ሲከፍል ደግሞ እንዴት እንደሚከፍል ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ነው የሚከፍላችሁ ማለት ክፍያችሁ በሰማያዊ ምንዛሪ ነው ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች እኔ የራሴን ስራ ነው የምሰራው ማንን ነው ማገልገል ያለብኝ የሚል ይኖራል፡፡
አንተ ደግሞ የምታገለግለው አገልግሎት የምትሰጠውን የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የንግድ ድርጅት ካለህ የምድር ጌቶችህ ካንተ የሚገዙና ላንተ የሚሸጡ በንግድ ለምትገኘው ማንኛውም ሰው ሁሉ የጌታን መልካምነት ማሳየትና በቅንነት ልታገለግላቸው ይጠበቅብሃል፡፡
ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ቆላስይስ 3፡23
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ክህንነት #ምስክር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment