Popular Posts

Wednesday, September 21, 2016

ከሐዲ ልብ

ንድን ሰው አይታችሁዋል፡፡ እግዚአብሄርን ሲያመልክ የነበረ ሰው ፣ ጌታን አገልግሎ የማይጠግብ የነበረ ሰው ፣ እግዚአብሄርን በቀላሉ ያምን የነበረ ሰው ነገር ግን ሁሉም ነገር ጠፍቶበት እግዚአብሄርን ለቀላል ነገር ማመን ሲያቅተው ፣ የእግዚአብሄርን ሃይል ሲክድና ባለማመን ሲሞላ እግዚአብሄርን ማገልገል ሞኝነት ሲመስለው አይታችኋል?

መጠንቀቅ እንጂ እኔ እንደዚያ ልሆን አልችልም ማለት አያስፈልግም፡፡ ያም ሰው አንድ ቀን "እኔን አይመለከተኝም እኔ ልወድቅ አልችልም በጣም ሩቅ መጥቻለሁ" ሲል የነበረ ከመጠን ያለፈ መተማመን በራሱ የነበረው ሰው ነበር፡፡

እንደዚህ አይነት ሰው የወደቀበትን ውድቀት ስናይ ከዚህ በፊት ጌታን ተረድቶት እንደነበር እንጠራጠራለን፡፡ እውነቱ ግን ማንም ሰው ሊወድቅ ይችላል፡፡ ከዚህ ውድቀት አልፌያለሁ እኔን አይነካኝም ሊል የሚችል ሰው የለም፡፡

ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ "ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ" የሚለው፡፡ሮሜ 11:20

የልብ ችግር ከባድ ችግር ቢሆንም ነገር ግን መፍትሄ የሌለው ችግር አይደለም፡፡ ለዚህ የልብ ክፋት ችግር መፅሃፍ ቅዱስ ፍቱን መድሃኒት አለው፡፡
በመጀመሪያ ሰው እግዚአብሄርን የሚያስክደው ክፉና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ሊጠነቀቅ ይገባዋል፡፡ የሚወድቀው የማይጠነቀቅና "እኔ ከመውደቅ አልፌያለሁ" የሚል ሰው ነው፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ ልባችን በጥንቃቄ የምንከታተለው እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ልባችንን በቸልታ ከያዝነው ሊያስተን የሚችል ትልቅ ሃይል ያለው ነው፡፡
ጌታን ብዙ ዓመት ከተከተልንና ካገለገልን በኋላ አንዳንዴ በልባችን የምናገኘው ክፉ ሃሳብ እኛን ራሳችንን ያስደነግጠናል፡፡እንደዚህ አይነት ሃሳብ ከእኔ ልብ ነው የወጣው ብለን አንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡

ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡19

የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? ኤርምያስ 17፡9

ልብን በጥንቃቄ መያዝ የሚበጀው ክፋት ሁሉ የሚወጣው ከልብ ስለሆነ ነው፡፡ ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ዕብራውያን 3፡12

የሰውን ልብ የሚያውቅውና ሊገራው የሚችለው የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው ወደ ልባችን ሊደርስ የሚችለው፡፡ በልባችን ያለውን ነገር ሁሉ እንደ እንደእግዚአብሄር ፈቃድ የሚያሳየንና የሚያስተካክለው የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ፊት ሁሉ ነገር የተገለጠና የተራቆተ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። ዕብራውያን 4፡12-13

ስለዚህ ነው ከምንም ነገር በላይ የእግዚአብሄርን ቃል ለመስማት መትጋት ያለብን፡፡ ስለዚህ ነው ልባችንን በንፅህና ለመጠበቅ ማድረግ ያለብንን ነገር ሁሉ ማድረግ ያለብን፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ "አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና" የሚለው፡፡ ምሳሌ 4፡23

ስለዚህ ነው የእግዚአብሄር ቃልን ከሚያስቡና ከሚናገሩ ሰዎች ጋር በየእለቱ ህብረት ማድረግና መመካከር ክፉና የማያምን ልብ እንዳይኖረን መፍትሄ እንደሆነ የሚናገረው፡፡ ስለዚህ ነው ህይወታችን የእግዚአብሄርን ቃል በሚረዱ ሰዎች ፊት መፈተን ያለበት፡፡

የእግዚአብሄርን ቃል የሚረዱ እህቶችና ወንድሞች ናቸው እኛ ያላየነውን የልባችንን ክፋት የሚነግሩንና ልብህ ንፁህ አይደለም ብለው የሚገስፁን፡፡ 
ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ ዕብራውያን 3፡13

ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ተመካከሩ #ከሃዲ #እልከኛ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

No comments:

Post a Comment