Popular Posts

Sunday, September 18, 2016

ኢየሱስ ጌታ ነው

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ጌታ ነው በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው በሚለው የሶስት ቃላት አረፍተ ነገር ውስጥ እጅግ የተጠቀጠቁ ትርጉሞች ይገኙበታል፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ሲባል
1. ኢየሱስ በሰማይ በምድር ከምድር በታች ሃያል ነው ማለት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡9-11
2. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞቱ የሻረ ብቸኛ የነገስታት ንጉስ ነው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ እስኪመጣ ድርስ ሞት ሃያል ጌታ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሞትን ያሸነፈ ማንም አልነበረም፡፡ ኢየሱስ ሲመጣ ግን በሞት ላይ ስልጣን ያለውን ሰይጣንን በሞቱ መሻሩን ያሳያል፡፡
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ ዕብራውያን 2፡14-15
3. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ሃይላትንና ስልጣናትን የገፈፈ የመጨረሻው ባለስልጣን ነው ማለት ነው ፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ኤፌሶን 1፡20-21
4. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ላይ መሪና ወሳኝ ነው ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በልባችን የመጀመሪያው ስፍራ የእርሱ ነው ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ከእርሱ ጋር የምናወዳድረው ምንም ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡ በልባችን ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ ነው ማለታችን ነው፡፡
ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡15 ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል እርሱን ከሁሉም በላይ እንወደዋለን ማለታችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል ከእርሱ ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡38-39
5. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል ከእጁ የሚነጥቀን ማንም ሃይል የለም በማለት እየተመካን ነው፡፡ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። ዮሐንስ 10፡29
6. ኢየሱስ ጌታ ነው ስንል በህይወታችን ላይ ጌታ ሊሆን የሚችለውን ነገር ሁሉ ላይ ጌታ ነው ማለታችን ነው፡፡
ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡38፣37
7. ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት የዳነው በኢየሱስ ጌትነት ነው ማለታችን ነው፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10
8. የምንሰብከው እንኳን ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን።
9. በቃልም ሆነ በስራ የምናደርገውን ሁሉ በጌታ ኢየሱስ ስም የምናደርገው ስለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ቆላስይስ 3፡17
10. በመጨረሻም የምንነግሰው የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ነው፡፡
እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ። ራእይ 7፡14 ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ንጉስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment