Popular Posts

Friday, August 19, 2016

ጽድቅን የሚጠሙ

ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ማቴዎስ 5፡6
በሃጢያት በወደቅን ጊዜ እግዚአብሄርን የማንፈልግ ነበርን፡፡ በሃጢያት በነበርን ጊዜ ለእግዚአብሄር መንግስት ፍላጎት ያልነበረን እግዚአብሄርን የማንፈልግ ነበርን፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የመዳኛ መንገድ ወደ እግዚአብሄር መንግስት በገባን ጊዜ ብቻ ነው ወደ ጤናማ መንፈሳዊ ህይወታችን የተመለስነው፡፡
በተፈጥሮ አንዱ የጤናማነት ምልክት ራብና ጥማት ነው፡፡ የታመመ ሰው የረሃብ ፍላጎቱ ይቀንሳል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የሞተ ፍጹም ረሃቡና ጥማቱ ይጠፋል፡፡
እንዲሁም የሰው የመንፈሳዊ ጤንነት ምልክቱ የእግዚአብሄርን ፅድቅ መራብና መጠማቱ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ትክክል ሆኖ ለመገኘት ያለንን ፍላጎታችንን ካጣነው በሆነ መንፈሳዊ በሽታ ተይዘናል ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ፅድቅ በጠገብንና ምንም ነገር እንደማያስፈልገን ባሰብን ጊዜ ማደግና መለወጥ እናቆማለን፡፡ ፅድቅን መራብና መጠማት ባቆምን ጊዜ ሁሉ እየደከምንና እየሞትን እንሄዳለን፡፡ በፅድቅ ለሚመክረው ለእግዚአብሄርን ቃል ቸልተኛ ከሆንን በመንፈሳዊ ችግር ውስጥ ወድቀናል ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16-17
ፅድቅን መራብና መጠማት በእግዚአብሄር መንግስት አንደኛው የጤንነት ምልክት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ይበልጥ መፈለግ በረከት ነው፡፡ ይበልጥ ለእግዚአብሄር ለመኖር የማጠማ ሰው የተመሰገነ ሰው ነው፡፡
ይበልጥ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መቅናት በረከት ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ይበልጥ ነገራችንን ለመስጠት መቅናት ጤንነት ነው፡፡ ይበልጥ ራስን ለእግዚአብሄር ማስገዛት መፈለግ በመንፈሳዊ በሽታ ያለመጠቃት ምልክት ነው፡፡ ለእግዚአብሄርና ለእግዚአብሄር ብቻ ለመኖር መፈለግ ጤንነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ ከጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ነው፡፡
ሌሎችን ነገሮች መራብና መጠማት የጤንነት ምልክት ላይሆን ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ መራብና መጠማት ግን ያለጥርጥር የጤነኝነት ምልክት ነው፡፡ ሌላውን ጥማታችንን እንደሚረካ እርግጠኛ ላንሆን እንችላለን፡፡ ይህንን ጥማታችንን ግን እግዚአብሔር ራሱ እንደሚያረካው እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን፡፡ የትኛውም ረሃባችን ባይረካ ይህ ረሃባችን ግን ሳይረካ አይቀርም፡፡
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
#ረሃብ #ጥማት #ጽድቅ #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

No comments:

Post a Comment