Popular Posts

Thursday, August 18, 2016

የእግዚአብሔር ምክር ይፀናል!

በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረውን ነገር ሁሉ የፈጠረው በአላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራውን ነገር ሁሉ የሚሰራው በእቅድ ነው፡፡
እግዚአብሄር እንዳመጣለት የሚኖር አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ ለሚሆነው ለእያንዳንዱ ነገር ሁሉ እቅድ አለው፡፡ እግዚአብሄር እጁን አጣጥፎ የሚሆነውን እያየ አይደለም፡፡
ሰዎች ውስን ስለሆንንና ሁሉንም ነገር ማድረግ ስለማንችል ብለን ብለን ሲያቅተንና ከአቅማችን በላይ ሲሆን ዳግመኛ መሞከር ከንቱ ሲሆንብን ለቀን እንነዳለን፡፡ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም እንላለን፡፡
የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን። ሐዋሪያት 21፡14
እግዚአብሄር ጀማሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ ስለሚሆነው ነገር የመጀመሪያው መሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ እንዲሆንለት የሚፈልገውም ነገር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ነው ኢዮብ ሞከረ ሞከረና ከእግዚአብሄር ሃሳብ ጋር መጋፋት እንደማይችል ሲረዳ ለእግዚአብሄር እንዲህ አለ፡፡ ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ኢዮብ 42፡1-2
ስለዚህ ሰው በልቡ ያለውን ምርጥ ሃሳብ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ የእግዚአብሄር ሃሳብ አግኝቶ ማድረጉ ይመረጣል፡፡ ከሰው ልጆች እጅግ የተሻለ አሳብ ይልቅ የእግዚአብሄር አሳብ ይበልጣል፡፡ እጅግ ታላቅ ከተባለው የሰው አሳብ ይበልጥ የእግዚአብሄር ምክር ትበረታለች በምድር ላይ ትሆናለች፡፡
ሰው ጠቢብ የሚሆነው የሰውን የተሻለ አሳብ በማግኘት ሳይሆን የእግዚአበሄርን ምክር በመፈለግ ነው፡፡ ለሰው ብልህነቱ የሰውን አስገራሚ አሳብ መፈለጉ ሳይሆን ታዋቂና ዝነኛ ያልሆነችውን የእግዚአብሄን ፈቃድ መከተሉ ነው፡፡
ለሰው አስተማማኙና ተመራጩ ነገር ሰዎች ሁሉ በአንድ ድምፅ የተስማሙበትን ምርጥ አሳብ ለማድረግ መፍጨርጨሩ ሳይሆን የእግዚአብሄርን አሳብ መከተሉ ነው፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ በዚያ ሁሉ ክብሩ ስለእውነት ሃያልነት እንዲህ እያለ ይመክረናል፡፡
ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልም 2ኛ ቆሮንጦስ 13፡8
እውነት በራስዋ ሃያል ነች፡፡ እውነት ምንም ደጋፊ አትፈልግም፡፡ ከእውነት ጋር የምንወግነው ለራሳችን ብለን ነው፡፡ ሰው የተሻለ ጠቢብ ከሆነ እውነትን ፈልጎ በእውነት ይተገናል እንጂ እውነትን ለመለወጥ አንድ እርምጃ አይራመድም፡፡ ሰው ብልህ ከሆነ እውነትን ፈልጎ ማድረጉ ከብዙ ትግልና መላላጥ ያድነዋል፡፡ የትኛውንም ያህል ሃያልነት ቢሰማን የእግዚአብሄር ምክር ላይ አንበረታም፡፡
ምንም ብንበረታ የእግዚአብሄርን ምክር ለመለወጥ መሞከራችን ጠቢብ አያደርገንም፡፡ ሰው መፅናት ከፈለገ ከምትፀናው ከእግዚአብሄር ምክር ጋር መወገኑ ወደር የሌለው ብልህ ያደርገዋል፡፡
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
#የእግዚአብሄርምክር #የእግዚአብሔርፈቃድ #እግዚአብሔር #ህብረት #እምነት #የሰውአሳብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment