Popular Posts

Sunday, June 5, 2016

ገንዘብ የክፋት ስር አይደለም

ገንዘብ በንግድ አለም ሃሳብን መለዋወጫ መግባቢያ ቁዋንቁዋ እንጂ በራሱ ክፉም አይደለም የክፋት ስርም አይደለም፡፡ ነገር ግን ገንዘብን መውደድ በእርግጥ የክፋት ስር ነው፡፡ የገንዘብ ፍቅር ካለብን ምንም ክፋትን ልናደርግ እንችላለን፡፡ ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል ካልሆነና ገንዘብን የምንወድ ከሆንን ከሌላ ከምንም ነገር ጋር ያለን ግንኙነት ይዛባል ትክክልም ሊሆን አይችልም፡፡
ገንዘብን መውደድ ግን ምንድነው?
ገንዘብን መውደድ ማለት ከሆነው በላይ ከፍ ያለ ግምት ለገንዘብ መስጠት ነው፡፡ ገንዘብም መውደድ ገንዘብ የህይወት ቁልፍ እንደሆነ ማሰብና ገንዘብ ሁሉን ነገር ሊገዛ እንደሚችል ማሰብ ነው ፡፡ ገንዘብን መውደድ የገንዘብን ትርጉምና አስፈላጊነትን አጋኖ እስከ ማምለክና ለገንዘብ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ እስከ መወሰን መድረስ ነው፡፡
ገንዘብን መውደድ የሚመጣው የገንዘብን ውስንነት ካለማወቅ ነው፡፡ ገንዘብ በጣም ውስን ነው፡፡ ገንዘብ ሊያደርጋቸው የማይችላቸው በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እንዲያውም በጣም ብዙ ውድ የሆኑ ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው በነፃ ከእግዚአብሄር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ባለጠጋ በብልጥግናው እንዳይመካ ድሃም ደግሞ በድህነቱ እንዳይዋረድ የሚያስተምረው፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ኤርምያስ 9፡23
ምክኒያቱም የህይወት ቁልፍ ያለው ባለጠግነት ውስጥ ሳይሆን እግዚአብሄር ጋር ነው፡፡ ነገር ግን የሚመካው። ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር። ኤርምያስ 9፡24
እንዲያውም እየሱስ ሲያስተምር የሰው ህይወቱ ትልቅነትና ትንሽነት በገንዘቡ ብዛትና ማነስ እንዳይደል ያስተምራል፡፡ የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ሉቃስ 12፡15
የገንዘብ ፍቅር በህይወታችን ያለንን ዋጋ አሰጣጥ ያዛባል፡፡ በገንዘብ ላይ ያለን ዋጋ አሰጣጥ ከተበላሸ በሌላ በሁሉም ነገሮች ላይ ያለን ዋጋ አሰጣጥ የተበላሸ ይሆናል፡፡
ገንዘብን የምንወድ ስንሆን በመጀመሪያ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ይበላሻል፡፡ ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ሲበላሽ ከእግዚአብሄር ጋር ላለን ግንኙነት ዋጋ አንሰጠውም፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
በመቀጠል ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ከተበላሸ ከራሳችን ጋር ያለን ግንኙነት ይበላሻል፡፡ ራሳችንን እግዚአብሄር እንደሚያየን ማየት ያቅተናል፡፡ገንዘብን ስናከብር ራሳችንን እንንቃለን፡፡
በመጨረሻም ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ከተበላሸ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ይበላሻል፡፡ ለሰዎች የሚገባቸውን ክብር መስጠት ይሳነናል፡፡ ሰዎችን የምንፈልጋቸው ለራሳችን ጥቅም ብቻ ይሆናል፡፡ ሰዎችን የምናየው ለኛ ጥቅም እንደተሰሩ ነገሮች ይሆናል፡፡ ገንዘብን ከወደድን ሰዎችን እንንቃለን እንጠላለን፡፡
መዋሸት ማታለል መሰረቅና ብሎም መጥላትና መግደል ገንዘብን የሚወድ ሰው ባህሪው ነው፡፡ ገንዘብን የሚገባውን ስፍራ ካልሰጠነውና ከሚገባው በላይ ካጋነንነው የክፋት ሁሉ ምንጭ ይሆንብናል፡፡
ገንዘብን መውደድ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ፡ ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነትና ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ያሳንስብናል ዋጋ ያሳጣብናል፡፡
ስለዚህ ገንዘብን አንውደድ
ይልቁንም እርሱም መልሶ። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ሉቃስ 10፡27
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

No comments:

Post a Comment