Popular Posts

Wednesday, June 15, 2016

ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል

እግዚአብሄር ታላቅ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ታዕምራትን የሚያደርገው ብቻውን ነው ፡፡ አሁን ያለንበት ደረጃ ከጥቂት አመታት በፊት ተራራ የነበረብን የክርስትናና የአገልግሎት ደረጃ ነው፡፡ አሁን ግን ደርሰንበታል እየኖርነው ነው፡፡ አሁን የምናስባቸው ተራራ የሆኑብን ነገሮች ደግሞ እንዲሁ በእግዚአብሄር ይደረስባቸዋል፡፡

የእስራኤል ህዝብ በጦርነት ላይ በነበረ ጊዜ በምድረበዳ ለራሳቸውና ለከብቶቻቸው የሚጠጡት ባለማግኘታቸው በህይወታቸው እጅግ ተጨንቀው ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን በነቢዩ በኩል እንዲህ ሲል ተናገራቸው፡፡

እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 1 ነገስት 3፡17

እግዚአብሄር በታእምራት ሊያኖረን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ታእምራትን ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ ደግሞም ለእግዚአብሄር ታእምራትን ማድረግ ድንቅ አይደለም፡፡

ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ 1 ነገስት 3፡18

እግዚአብሄር ታዕምራትን ለማድርግ እጅግ መዘጋጀትና ብዙ ምልክቶችን ማድርግ አይጠበቅበትም፡፡ ምልክቶች እንኳን ባይኖሩም እግዚአብሄር ከመቀፅበት ታዕምርን ለማድረግ ይችላል፡፡

ግን ሁሌ የእኛን ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ጌታ እንዲያውም ጊዜ የሚወስድው እኛን በማዘጋጀት ስራ ላይ ነው እንጂ ታዕምር የማድርግ ስራ ላይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የእስራኤል ህዝቡ አስቀድሞ እንዲዘጋጁ እግዚአብሄር በነቢዩ እንዲህ አለ፡፡

እንዲህም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፍሩ። 1 ነገስት 3፡16

ለምን ? ታዕምራቱ ሲመጣ ውሃው ሲመጣ ውሃውን መያዣ ጉድጉዋድ ከሌለ ታዕምራቱ ለታቀደለት ጊዜ ሊቆይና በታቀደለት አላማ ላይ ሊውል አይችልም፡፡ የእኛ ዋናው ድርሻ ተአምራቱን ማቆየትና የተአምራቱን ውጤት ለረጅም ጊዜ የመጠቀም ሃላፊነት ነው፡፡

ይህ የእግዚአብሄር ሃላፊነት በፍፁም አይደለም፡፡ ይህን ታእምራቱን አቆይቶ ለታለመለት አላማ ማዋል የሰው ድርሻ ነው፡፡ ስለዚህ የታዕምራቱን መምጣት ስንጠብቅ በትጋት እንዘጋጅ፡፡
የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ምሳሌ 16:1

Abiy Wakuma Dinsa
#amharic #ethiopia #spiritual #christian #jesus 

No comments:

Post a Comment