Popular Posts

Saturday, June 11, 2016

የህይወት መንፈስ

እየሱስን አዳኛችን እና የህይወታችን ጌታ አድርገን ከተቀበልነው ቅፅበት ጀምሮ እየሱስ በእኛ ውስጥ መኖር ይጀምራል፡፡
እየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ በእግዚአብሄር አብ እየተመራ እግዚአብሄርን አስደስቶታል፡፡ አሁንም እየሱስ በውስጣችን የሚኖረው እርሱ በምድር ቆይታው እግዚአብሄርን ደስ እንዳሰኘ እኛም እንዴት እግዚአብሄርን ደስ እንደምናሰኝ ሊያስተምረን ሊመራን ነው፡፡
በውስጣችን መለኮታዊ ህይወት አለ፡፡ በውስጣችን እየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ይኖራል፡፡
በውስጣችን ያለውን እየሱስን በሚገባ ከተከተልን እግአብሄርን በኑሮዋችን ማስደሰት እንችላለን፡፡
እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡27
እግዚአብሄር ከእኛ የሚፈልገው በራሳችን አነሳሽነት ይህን ይፈልጋል እያልን እየገመትን እንድኖር በፍፁም አይደለም፡፡ ወይም ክፉና ደጉን እንደምታሳውቀው ዛፍ አትቅመስና አትንካ በሚሉ ትእዛዞች እንድኖር አይደለም፡፡
ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ቆላስይስ 2፡20-22
በውስጣችን ያለው የእግዚአብሄር ህየወት አንድን ነገር ለማድረግ ሲነሳሳ አብረነው ካደረግን በውስጣችን ያለው ህይወት አይሆንም እንቢ ሲለን ካቆምን በውስጣችን ያለው ህይወት ቆይ ጠብቅ ሲለን ከጠበቅን ልባችንን በመከተል እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት እንችላለን፡፡
እግዚአብሄር ሁል ጊዜ ይመራናል፡፡ ልጆች እርግጠኛ ካልሆኑ የአባታቸውን ፊት እንደሚያዩት እኛም በአስተሳሰባችን በንግግራችንና በድርጊታችን የእግዚአብሄርን የፈገግታ ፊትና የመኮሳተር ፊት በልባችን ውስጥ ልንፈልግ ይገባናል፡፡
በውስጣችን ያለውን ህይወት ከተከተልን እግዚአብሄርን እንደምናስደስት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲያውም ውስጣችንን ከመከተል የበለጠ እግዚአብሄርን ማስደሰቻ ሌላ አስተማማኝ መንገድ የለም፡፡
ውስጣችንን ካልተከተልን ግን ምንም ያህል ያወቅን ቢመስለንና ሰውኛ ምክኒያቶች ቢኖሩን ከእግዚአብሄር ጋር እንተላለፋለን፡፡

No comments:

Post a Comment