Popular Posts

Follow by Email

Friday, January 19, 2018

እንኳን ለጥምቀት ህይወት አደረሳችሁ

ጥምቀት በአመት አንድ ቀን የምናስታውሰው በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ህይወት ነው፡፡ ጥምቀት የክርስትና ህይወይ ዘይቤ ነው፡፡
ኢየሱስ የሞተውና የተነሳው ስለእኛ ሃጢያት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተውና የተቀበረው እኛን ወክሎ ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተውና የተቀበረው በእኛ ፋንታ ነው፡፡  
ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እንደሞተና እንደተቀበረ እውቅና ስንሰጥ በውሃ እንጠመቃለን፡፡ በውሃ የመጠመቃችን ትርጉሙ ኢየሱስ ስለእኛ እንደሞተ እንደተቀበረ ማሳይ ነው፡፡ በውሃ የመጠመቃችን ትርጉሙ ኢየሱስ ስለሃጢያቴ እንደሞተልኝ እኔም ለሃጢያትና ለአለም ክፉ ምኞት ሞቻለሁ ማለት ነው፡፡  
ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ሮሜ 6፡3
በውሃ ስንጠመቅ ከውሃ ስር እንድምንሆንና ውሃው እኛንና ሌላውን አለም እንደሚለይ ሁሉ የጥምቀት ምሳሌነቱ ከሃጢያት መገላገላችንና መለያየታችን ሃጢያት እንደማይገዛንና ከሃጢያት ሃይል ነፃ መውጣታችን ማሳያ መንገድ ነው፡፡
እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሮሜ 6፡4
ጥምቀት ከሃጢያት ሃይል ነፃ የወጣንበት የእግዚአብሄር አሰራር እንጂ የሃጢያት በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ቅድስናን የተቀበልንበት የእግዚአብሄር አሰራር እንጂ ሃጢያት የሚነግስበት በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ከሃጢያት ሃይል ነፃ የወጣንበት አሰራር እንጂ ሃጢያት የሚስፋፋበት በአለ አይደለም፡፡ ጥምቀት እግዚአብሄር የሚፈራበትና የሚከበርበት በአል እንጂ የሰይጣን ስራ ሃጢያትና እርኩሰት የሚስፋፋበት በአል አይደለም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥምቀት #ሞት #ትንሳኤ #መቀበር #አዲስህይወት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Thursday, January 18, 2018

እምነት ይጠይቃል

ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሰምር እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ማንኛውም ግንኙነት መንፈሳዊውን አለም የእግዚአብሄርን መንግስት ማየት ይጠይቃል፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ለመኖር በመካከላችን ያለችውን በአይን የማትታየውን መንፈሳዊውን አለም ማየት ይጠይቃል፡፡
ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡21
መንፈሳውን አለም ማየት የማይችል ሰው ከእግዚአብሄርም ጋር ይሁን በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ አለም ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም፡፡ በተፈጥሯዊ አይንህ የሚታየውን ነገር ብቻ የሚያይ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሊግባባ ፣ አብሮ ሊሰራና ውጤት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለመንፈሳዊ አለም አይኑ የታወረ ሰው እግዚአብሄርን ሊያየው እና ሊከተለው አይችልም፡፡  
ስለዚህ ነው ካለእምነት አግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው፡፡ እግዚአብሄርን ለማሰደስት እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር እኛን በሚያስደንቁን ብዙ ነገሮች አይደነቅም፡፡ እኛን የሚያስደስቱን ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን ላያስደስቱት ይችላሉ፡፡ እምነት ግን በእርግጥ እግዚአሔርን ደስ ያሰኘዋል፡፡
ሰው በምድር የሚፈለጉት ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ሁሉ ቢኖረው እምነት ግን ከሌለው እግዚአብሄርን አያስደስተውም፡፡ ጠቢብ ይሁን ያልተማረ ፣ ሃያልም ይሁን ደካማ ፣ ባለጠጋም ይሁን ደሃ እግዚአብሄርን የሚያሰደስተው ጠብቡ ሃይሉ ባለጠግነቱ ሳይሆን እምነቱ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሰው ጥበብ አያበረታታውም ፣ እግዚአብሄርን የሰው አለማወቅ ተስፋ አያስቆርጨውም ፣ የሰው ሃይል አያስገርመውም የሰው ድካም አያስደነግጠውም ፣ የሰው ባለጠግነት አያስገርመውም የሰው ድህነት አይከብደውም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
የሰው ጥበብ ምንም እንደማያመጣ ፣ የሰው አለማወቅ ምንም እንደማይቀንስ ፣ የሰው ሃይል ከቁጥር እንደማይገባ ፣ የሰው ድካም ነገሩን እንደማይለውጥ ፣ የሰው ባለጠግነት ምንም እንደማይጨምር ፣ የሰው ድህነት ምንም እንደማይቀንስ ማወቅና ሁሉን በሚችል በእግዚአብሄር መታመን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡  
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
የሰው ፈጣንነት እግዚአብሄርን አያንቀሳቅሰውም፡፡ እግዚአብሄርን የሚያንቀሳቅሰው እምነት ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ወደእግዚአብሄርን በእምነት የሚደርስ ሰው ከእግዚአብሄር ዋጋን ይቀበላል፡፡ በእምነት ከእግዚአብሄር ጋር የሚገናኝ ሰው በእግዚአብሄር ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ይኖራል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ዋጋ #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, January 17, 2018

እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል

ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። 1ኛ ዮሐንስ 4፡11-12
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ የፍቅር ህይወት እግዚአብሄርን ይስበዋል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ለመኖርና ለመስራት ፍቅር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በፍቅር ይኖራል፡፡ የፍቅር ህይወት ለእግዚአብሄር ተስማሚ ቤቱ ነው፡፡ ፍቅር ለእግዚአብሄር የፈለገውን መልካምነት ዘርቶ የሚያጭድበት ተስማሚና ለም መሬት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰዎችን ለመባረክ በፍቅር የሚኖርን ሰው ይጠቀማል፡፡ በፍቅር ያልሆነ ነገር እግዚአብሄርን ይገፋዋል፡፡ በፍቅር የሆነ ህይወት እግዚአብሄርን ይጋብዘዋል፡፡ እግዚአብሄር ካለ ደግሞ መልካመ ነግር ሁሉ ይኖራል፡፡ እግዚአብሄር ሲኖር ህይወት ይትረፈረፋል፡፡    
እንዲሁም ጥላቻ ደግሞ ለሰይጣን ለም መሬቱ ነው፡፡ ሌባው ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ስለሌላ አይመጣም፡፡ ሰውን ለመስረቅ ለማረድና ለማጥፋት ከመጠቀሙ በፊት ሰይጣን ጥላቻን በሰው ውስጥ ይልካል፡፡ ሰው የጥላቻን ሃሳብ ከተቀበለና ጥላቻ ውስጥ ከገባ ሰይጣን በቀላሉ የመስረቅ የማረድና የማጥፋት ተልእኮውን ሊያሳካ ይችላል፡፡
ሰው በልቡ ጥላቻ ከሌለበት ደግሞ ሰይጣን በምንም መልኩ በሰው ሊጠቀም አይችልም፡፡ሰው በፍቅርና በምህረት ከተመላለስ ሰይጣን በህይወታችን መቆሚያ ቦታ ያጣል፡፡  
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27
በግቢያችን ዝንብ እንዳይገባ ከፈለግን ዝንብን የሚስበውን ቆሻሻ ማፅዳት ወሳኝ አለብን፡፡ ዝንብ መጥቶ የሚያርፍበትና የሚላው ቆሻሻ ከሌለ ይራባል ለመኖር ያቅተዋል፡፡ ስለዚህ የዝንብ ማስወገጃ ተዘዋዋሪ መንገድ ቤትን ከቆሻሻ ማፅዳት ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሰይጣን በህይወታችን እንዲቆይ የሚያደርገው የሚበላው ቆሻሻ ነገር ጥላቻን በህይወታችን ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ህይወታችን ከጥላቻ ከፀዳ ግን ቢመጣም የሚበላው ነገር ስለማያገኝና ስለሚራብ መቀመጥ አይፈልግም፡፡ ከጥላቻ የፀዳ አእምሮ ለሰይጣን አመቺ ስፍራ አይደለም፡፡ ከጥላቻ ራሱን የሚጠብቅ ሰውና ከጥላቻ የራቀ ህይወት ለሰይጣን ምንም ተዘርቶ የማይበቅልበት ጭንጫ መሬት ነው፡፡
ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። 1 ዮሐንስ 411-12
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ  #ፍቅር #መውደድ #እግዚአብሔር #ፍፁም #እርስበርስ #ተግባር #ትጋት #ስራ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #እምነት #ምህረት #ይቅርታ #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ

Tuesday, January 16, 2018

እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው

እግዚአብሄር ጠቢብ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን በድንገት አልፈጠረውም፡፡ እግዚአብሄር እየፈጠረ እያለ እንደ ድንገት ሰው የሚባል ፍጥረት አልፈጠረም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ሰው እንዴት እንደሚሆን ፣ ምን እንደሚኖረውና ምን ምን እንደሚያደርግ ያውቅ ነበር፡፡
እንዲያውም እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረበት ምክኒያት ሰው በምድር ላይ የሚያደርገው ስለነበረ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረበት ምክኒያት ለአላማው ሰውን አይነት ፍጥረት ስለፈለገ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረበት ምክኒያት የሰው አይነት ፍጥረት ብቻ ሊሰራው የሚችለው አላማ ስለነበረው ነው፡፡  
እግዚአብሄር መጨረሻውን ከመጀመሪያ ያያል፡፡ እግዚአብሄር ድንገት የሚመጣለትን ሃሳበ የሚያደርግ አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው እንዲሁም እግዚአብሄር ለአላማው ጨካኝ ነው፡፡
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። ኢሳያስ 46፡10
እያንዳንዳችን ወደምድር የመጣነው በስማችን የተለየ አላማ ስለነበረ ነበር፡፡ አብሮን የተፈጠረው ክህሎትና ስጦታ ለዚያ አላማ ማስፈፀሚያ የሚውል ነው፡፡ እያንዳንዳችን ወደምድር የመጣነው እኛ ብቻ ልንሰራው የሚገባ የተለየ አላማ ስላለ ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር አላውን በምድር ላይ በትጋት እየሰራው ነው፡፡ እግዚአብሄር ለአላማው ጨካኝ ነው፡፡
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን አላማ ለማስፈፀም ተጨነቀ፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም ነፍሱ እስከሞት አዘነች፡፡ ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይሁን የእኔ ፈቃድ አይሁን በማለት ለእግዚአብሄር ዘላለማዊ አላማ ራሱን ሰጠ፡፡
እግዚአብሄርም የሰው ልጆች መዳን በኢየሱስ መስዋእትነት መፈፀም ስለነበረበት ኢየሱስ ለምን ተውከኝ እስከሚል ድረስ እግዚአብሄር ጨከነ፡፡  
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተሰፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, January 13, 2018

ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1 ዮሐንስ 5፡4
እግዚአብሄር የዘላለም ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር አሸናፊ ነው፡፡
አለም በመንፈሳዊ አለም በጦርነት የተሞላች ነች፡፡ በዚህ ምክኒያት ብዙ ሰዎች በአለም ተሸንፈው ቀርተዋል፡፡
አለምን የምናሸንፈው በእድል አይደለም፡፡ አለምን የምናሸንፈው በእውቀት አይደለም፡፡ አለምን የምናሸንፈው በሃይል አይደለም፡፡ አለምን የምናሸንፈው በብልጥግና አይደለም፡፡ የአለም አሸናፊነት የምድራዊ አሸናፊነት ጉዳይ አይደለም፡፡ አለም ከእግዚአብሄር ያልተወለዱትን አዋቂዎች ፣ ሃያላን እና ባለጠጎች ሁሉ አሸንፋ ከንቱ አድርጋለች፡፡
በአለም ላይ አሸናፊ ለመሆን ብቸኛው መንገድ ከእግዚአብሄር መወለድ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የተወለደ ሁሉ ደግሞ አለምን ያሸንፋል፡፡
ሰው በእምነት መንፈሳዊውን አለም ካላየና ከእግዚአብሄር ጋር በእምነት ካልተገናኘ አለምን መሸነፍ በፍፁም አይችልም፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ቃል ዳግመኛ በመወለድ ብቻ የእግዚአብሄርን መንግስት ማየትና ከንጉሱም ጋር መገናኘት ይችላል፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
ሰው በእምነት የዘላለሙንና የማይታየውን ካላየ በስተቀር አለምን ማሸነፍ አይችልም፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ሰው በእግዚአብሄር ቃል ጉልበት ካልሆነ አለምን ማሸነፍ አይችልም፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት በእምነት አይን ካላየ አለምን ማሸነፍ አይችልም፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ሰው ግን የሁሉ ነገር ምንጭ የሆነውን መንፈሳዊውን አለም ማየት ከቻለ አለምን ማሸነፍ ይችላል፡፡
ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ዕብራውያን 11፡3
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃያል #ጠቢብ #ባለጠጋ #ድልነሺ #ዳግመኛመወለድ #የእግዚአብሄርልጅ #መንፈስ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አሸናፊ #አለቅነት #ስልጣናት #ስልጣን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, January 12, 2018

ከሞተ ስራ ንስሃ

በመፅሃፍ ቅዱሳችን ውስጥ ካሉት ለሰመረ የክርስትና ህይወት መሰረት ከሆኑት መሰረታዊ ትምህርቶች መካከል ንስሃ አንደኛው ነው፡፡፡
ንስሃ ሃሳብን መለወጥ ሲሆን ሰው በፊት ከሚኖርነት የኑሮ አስተሳሰብ እእምሮው ተለውጦ በአዲስ አስተሳሰብ መኖር ሲጀምር ንስሃ ገባ ይቨባላል፡፡
ንስሃ መግባት ማለት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶችን ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ንስሃ ከምንሄድበት መንገድ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ መመለስ ነው፡፡ ሃሳባችንን ለውጠን ካልተመለስን በስተቀር የምናደርጋቸው ማንኛውም ሃይማኖታዊ ስርአቶች ሃይማኖተኛ እንደሆንን እንዲደሰማን ያደርጉ ይሆናል እንጂ ለእውነተኛ መንፈሳዊነት አይጠቅሙም፡፡ እግዚአብሄር መመለስን ይባርካል፡፡  
እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። ሐዋርያት 3፥19-20
በአለማችን ላይ በአስተምሮት ትምህርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ያስነሳቸው የመፅሃፍ ቅዱስ አስተማሪው ዴሪክ ፕሪንስ ሲናገሩ በክርስትና ህይወት ላለማደግና ላለመለወጥ ትልቁ ፈተና ንስሃ አለመግባት ነው ይላሉ፡፡ እንዲሁም በቤተክርስትያን ውስጥ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ንስሃ ያልገቡ ሰዎች ናቸው ይላሉ፡፡
ሰው በአለም አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊሰራ ሲሞክር ሁሉ ነገር ይዛባበታል፡፡ የአለም ሃሳቡን ለመተው ያልተዘጋጀ ሰው አብረው በፍፁም የማይሄዱ ሁለት ነገሮችን አብሮ ሊያስኬድ በመሞከር ህይወቱን ያጠፋል፡፡ የማንስሃ ንስሃ ያልገባው ሰው የሚፈልገውን ነገር ቢያገኝ እንኳን የእግዚአብሄርን አብሮነት በህይወቱ ያጣዋል፡፡
ጌታን የተቀበልነው ይህ አስተሳሰቤና ኑሮዬ አያዋጣኝም ብለን ነው፡፡ ነገር ግን ጌታን የተቀበለው ለሃይማኖት ለውጥ ከሆነ ምንም ውጤት ሳናገኝ ህይወችንን አናባክናለን፡፡
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ኤፌሶን 4፥22-23
አንድ ጊዜ እንደዚህ ሆነ፡፡ አንድ እህት ስለአንድ አገልጋይ እየነገረችኝ ነበር፡፡ ይህ አገልጋይ በጌታ ባይሆን ኖሮ ስንት ሴቶችን ያማርጥ እንደነበረ የነገራትን ስትነግረኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ አልነገርኳትም እንጂ በልቤ ይህ ሰው ንስሃ አልገባም ህይወቱ አደጋ ላይ ነው አልኩ፡፡
ይህ በቤተክርስትያን ውስጥ በጣም ሲያገለግል የነበረው እግዚአብሄር ያስነሳው አገልጋይ ከአመታተ በኋላ ወደኋላ ተመለሰና ያ ሲመካበት የነበረውን ሃጢያት ማድረግ ጀመረ፡፡ ወደ ቤተክርስትያን መጥቶ ነበር እንጂ የሃጢያት ጣእም በአፉ ውስጥ ነበር፡፡ ሃጢያትን አልተፀየፈውም አላፈረበትም ነበር፡፡
እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። ሮሜ 6፥21
ያለውን ማንኛውም አስተሳሰብ ለእግዚአብሄርን ቃል ለመለወጥ የወሰነ የተሰበረ ሰው በቤተክርስትያን ሲያድግና ሲለወጥ ታያላችሁ፡፡
በአስተሳሰባችን አለምን መስለን እግዚአብሄር ይባረከናል ብሎ መገመት ራስን መታለል ነው፡፡ ስለዚህ ነው በአለም አስተሰሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ስለማይሳካልን መፅሃፍ ቅዱስ አስተሳሰባችሁንና አካሄዳችሁን ለውጡ ንስሃ ግቡ የሚለን፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፥2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #ኢየሱስ #ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መንገድንመቀየር #አስተሳሰብንመቀየር #መለወጥ #በረከት #መታደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህ - ከውስጥ ወደ ውጭ የሆነ ክንውን

ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። 3 ዮሐንስ 1፡2
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በለመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለክንውን ነው፡፡ እግዚአብሄር ለውድቀት የፈጠረው ሰው አልነበረም፡፡
ሰው በሃጢያት ምክንያት ክንውንን ከህይወቱ አጣው፡፡
ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ ለመክፈልና የእግዚአብሄር ልጅነትን ክንውን በህይወታችን ሊመልስ ነው፡፡
እውነተኛ ክንውን ደግሞ የሚጀምረው ከውስጥ ነው፡፡ ሰው ሲከናወንለት መጀመሪያ በነፍሲ ይከናወንለታል፡፡ በውጭው የሚከናወንለት ሰው ተከናወነለት አይባል፡፡ ነፍሱ ያልተከናወነችና በነፍሱ የተቀብዘበዘ ክንውኑ የውሸት ክንውን ነው፡፡ እግዚአብሄር ውጫችን እንዲከናወን የሚፈልገው የውጭውን ክንውን የሚሸከመው ውስጣችን በተከናወነ መጠን ነው፡፡ የውጭውን ክንውን የሚያስተዳደረው የውስጣችን ባህሪያን በተሰራና ባደገ መጠን ውጫችን እንዲከናወን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡  
ታላቁና ክንውን የነፍስ ክንውን ነው፡፡ ታላቁ ክንውን የነፍስ ነፃ መውጣት ነው፡፡ ትልቁ ክንውን የነፍስ ከጥላቻ ከመራርነት ከመቅበዝበዝ ነፃ መውጣት ነው፡፡
የነፍስ ክንውን መገለጫዎች
ፍቅር
በፍቅር የሚመላለስ ሰው እውነተኛ የተከናወነለት ሰው ነው፡፡ በጥላቻ የሚኖር ሰው በእስራት ይኖራል፡፡ በጥላቻ የሚኖር ሰው በጨለማ ይኖራል፡፡ በጥላቻ የሚኖር ሰው በስቃይና በጉስቁልና ይኖታል፡፡  
እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 4፡16
ሰላም
ሰው ሰላም ካለው ሃብታም ነው፡፡ ሰላም የሌላው ሰው ምንም ቢኖረው ጎስቋላ ነው፡፡ ሰው ሰላም ከሌለው ደካማ ነው አቅምም የለውም፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15
እርካታ
ሰው ባለው ነገር ካልረካ በጉድለት ይኖራል፡፡ ሰው ባለው ነገርና በደረሰበት ደረጃ ራሱን ካማጠነና ከረካ በነፃነት ይኖራል፡፡
ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2 ቆሮንቶስ 6፡4
ደስታ
የልብ ደስታ የሌለውና የሚያዝን ሰው ደካማ ይሆናል፡፡ የልብ ደስታ ሃይላችን ነው፡፡ ሰው በጌታ ያለው ደስታ ከምንም ሃዘን በላይ ከሆነ እንዳይጎዳ ይጠብቀዋል፡፡ ሰው በምድራዊ ማግኘትና ማጣት ደስታው ከፍና ዝቅ የማይል ሰው የተከናወነለት ሰው ነው፡፡   
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
ምሪት
ምሪት ያለው ሰው የት እንዳለ ወደየት እንደሚሄድ የሚያውቅ ሰው ብርሃን አለው፡፡ ሰው ግን የሚሄድበትን ካላወቀ ሲደርስም አያውቅም፡፡ ሰው የሚሄድበትን ካላወቀ መቼ እንደሚሰናከል አያውቅም፡፡
ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል። ምሳሌ 19፡2
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡17-19
የልብ ንፅህና
ሰው መሃሪና ይቅር ባይ ካልሆነ አልተከናወነለትም፡፡ ልቡ ንፁህ ላልሆነ ሰው እውነተኛ ክንውን የማይታሰብ ነው፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
እምነት
ሰው እግዚአብሄርን ካመነ የተከናወነለት ሰው ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። እብራዊያን 11፡6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #ደስታ #እርካታ #ሰላም #ምሪት #ፍቅር #እምነት #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #የልብስፋት #ማስተዳደር #እረፍት